ምድብ ስምንት፡ፖላንድ፣ ሴኔጋል፣ ኮሎምቢያ እና ጃፓን

Sadio Mane Image copyright Getty Images

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ ስምንት

Image copyright Getty Images

ፖላንድ

የቀደመ ታሪክ፡ ፖላንድ በዓለም የፊፋ ደረጃ ስድስተኛ ላይ ተቀምጣለች። ሃገሪቱ የዓለም ዋንጫን አንስታ ባታውቅም ብዙዎች የአሁኑ ቡድን ጠንካራው እንደሆነ ይስማማሉ። ከዚህ ቀደም ያስመዘገቡት ትልቅ ውጤት ሶስተኛ ደረጃ ነበር። ይህንንም እ.አ.አ በ1974 እና 1982 ያሳኩት ነው።

ቁልፍ ተጫዋች፡ የባየር ሙኒኩ አጥቂ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በዘጠኝ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ጎሎችን አስቆጥሯል። የብሔራዊ ቡድኑም የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው። በ91 የብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች 51 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል።

አስልጣኙ ማን ናቸው? አዳም ናዋልካ እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ ብሄራዊ የቡድኑ አሰልጣኝ በመሆን 39 ጨዋታዎችን አከናውነዋል። ኮንትራታቸው ከአንድ ወር በኋላ የሚጠናቀቅ ቢሆንም ቡድኑን ለዩሮ 2016 አብቅተውታል። በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ መሳተፍ ባይችሉም ሁለተኛ ትልቅ ውድድራቸውን ቡድኑን በመምራት ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሴኔጋል

የቀደመ ታሪክ፡ ሴኔጋል ከ2002 ወዲህ የመጀመሪያዋ በታሪኳ ደግሞ ሁለተኛዋ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ይሆናል። በ2002 እስከሩብ ፈጻሜ ደርሳ ነበር በቱርክ 1 ለ 0 የተሸነፈችው።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ከ2012 ጀምሮ በ48 ጫወታዎች 14 ግቦችን ያስቆጠረው ሳዲዮ ማኔ ልምድ ያካበተ ተጫዋች ነው። በ2015 ደግሞ ሳውዝሃምፕተን አስተንቪላን 6 ለ 1 በረታበት ጨዋታ በ176 ሰከንዶች 3 ግቦችን በማስቆጠር በፕሪሚየር ሊግ ታሪክ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል። በ2016 በ 34 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ሊቨርፑል ሲዘዋወር በወቅቱ በከፍተኛ ገንዘብ የተዘዋወረ አፍሪካዊ ተጫዋች ሆኖ ነበር።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? አሊዩ ሲሴ የቀድሞ የሴኔጋል፣ የፖምፒይ እና የበርሚንግሃም ተጫዋች ናቸው። የአሁኑ የ41 ዓመት አሰልጣኝ በ2012 ለአጭር ጊዜም ቢሆን አማራ ትራኦሬ መባረራቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሚናን ተጫወተዋል። ከዚያም ከ2012-2013 ድረስ የሴኔጋልን ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ብድንን ሲያሰለጥኑ ቆይተው ወደዋናው ብሄራዊ ቡድን አቅንተዋል።

Image copyright AFP

ኮሎምቢያ

የቀደመ ታሪክ፡ ኮሎምቢያ በ2014 ብራዚል ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ምርጥ ቡድን ነበር ይዛ የቀረበችው። ለሩብ ፍፃሜ ሲደርሱ ከአዘጋጇ ብራዚል ጋር ተጋጥመው 2 ለ 1 ተሸንፈዋል። ጀምስ ሮድርጌዝ ሪያል ማድሪድ ውስጥ የነበረ ሲሆን ባለፉት የውድድር ዓመታት ሁለት ቻምፒየንስ ሊግን ማሸነፍ ችሏል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ጀምስ ሮደርጌዝ። ተጫዋቹ የአማካይ አጥቂ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ከሪያል ማድሪድ ወደ ባየር ሙኒክ በውሰት ሄዶ በመጫወት ላይ ይገኛል። በ2014 የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አግቢ በመሆን ተሸልሟል። በአለም ዋንጫው ስድስት ኳሶችን ከመረብ አዋህዷል።

አሰልጠኙ ማን ናቸው? ጆዜ ፒክርማን ከ2012 ጀምሮ የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ናቸው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ሶስት ጊዜ የደቡብ አሜሪካ ምርጥ አሰልጣኝ ለመባል በቅተዋል።

ጃፓን

የቀደመ ታሪክ፡ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በጥምረት ያዘጋጀችውን የ2002 (እአአ) የዓለም ዋንጫን ጨምሮ ጃፓን ሁለት ጊዜ በውድድሩ ለሁለተኛ ዙር ደርሳለች።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ኬሱኬ ሆንዳ፣ ሺንጂ ካጋዋ እና የሌስተሩ አጥቂ ሺንጂ ኦካዛኪ የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም ለብሔራዊ ቡድኑ ሦስት ጎሎችን ያስቆጠረውና ከአርሴናል በውሰት ባለፈው የውድድር ወቅት ለጀርመኑ ስቱትጋርት ተጫውቶ ቡድኑ ወደ ቡንደስ ሊጋ እንዲያድግ ወሳኝ አስተዋፅኦ ያደረገው ታኩማ አሳኖ ድንቅ ተጫዋች መሆኑ ተመስክሮለታል።

አሰልጣኙ ማነው? የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የፊት መስመር ተጫዋችና የፓሪስ ሴንዠርሜን፣ ዳይናሞ ዛግሬብ እና የአይቮሪ ኮስት አሰልጣኝ የነበሩት ቦሲኒያዊው ቫሂድ ሃሊልሆድዚች የአልጄሪያን ቡድን በ2014 ለጥሎ ማለፍ ደረጃ በማብቃት ታሪክ ሰርተዋል። አሁን ደግሞ የጃፓንን ቡድን እያሰለጠኑ ቢሆንም በቡድኑ ካምፕ ውስጥ አለመረጋጋት አለ የሚሉት ሪፖርቶች እውነት ከሆኑ የአሰልጣኝ ለውጥ ሊኖር ይችላል።