አሁንም ኢትዮጵያ ዜጎቿን በመሰለል ተከሳለች

አሁንም ኢትዮጵያ ዜጎቿን በመሰለል ተከሳለች Image copyright THINKSTOCK

የኢትዮጵያ መንግሥት የገዛ ዜጎቹ ላያ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ስለላ እያደረገ ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው የመብት ተሟጋች ድርጅት ወቀሰ።

የፖለቲካ መብት ተሟጋቾች እና ነፃ ድምፆች ላይ የሚያደርገውን ስለላም እንዲያቆም ድርጅቱ አሳስቧል።

ኅዳር 27/2010 የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ መብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚ አካላት ላይ ስለላ እያደረገ እንደሆነ መቀመጫውን ቶሮንቶ ያደረገ 'ሲትዝን ላብ' የተሰኘ የቴክኖሎጂ ተቋምን ጠቅሶ ድርጅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት መሰል ትችቶች ሲቀርቡበት የመጀመሪያው ባይሆንም አሁን ላይ ግን ስለላውን እጅግ አጠናክሮ ቀጥሏል ይላል ሪፖርቱ።

"የኢትዮጵያ መንግሥት ሃሳቡን የሚተቹ ዜጎች ላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል ይሁኑ ስለላ ከማድረግ አልተቆጠበም" ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ አጥኚ ሲንቲያ ዎንግ ይናገራሉ።

"መሰል ስለላዎች የሰዎችን ሃሳብ የመግልፅ ነፃነት፣ ግላዊነት እንዲሁም የዲጂታል ደህንነት ይፈታተናሉ" ሲሉ ያክላሉ አጥኚዋ።

ከ2016 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው ጥናት እንደሚጠቁመው ስለላው በርካታ የፖለቲካ መብት ተከራካሪዎችን ዒላማ ያደረገ ሲሆን በተለይ ደግሞ የኦሮሞ መብት ተሟጋቾች የስለላው ትልቅ አካል መሆናቸውን ድርጅቱ ያስታውቃል።

ከእነዚህም መካከል መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክ ኃላፊ ጃዋር መሐመድ አንዱ መሆኑ ታውቋል።

የኦሮሚያ ሚድያ ኔትዎርክን ለማገድ ብዙ ሙከራዎችን ማድረጉን ያወሳው ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹ መረጃ እንዳያገኙ እገዳ እያደረገ ነው ሲል ይወቅሳል።

የስለላው ተጠቂዎች በኤሌክትሮኒክ የመልዕክት መላላኪያ አድራሻቸው (ኢሜይል) በኮምፒውተራቸው ላይ የሚጫን ሶፍትዌር በመላክ የሰዎቹን የግል መልዕክት ማየት የሚያስችል ቫይረስ ተልኮላቸዋል።

ሶፍትዌሩን ኮምፒዩተራቸው ላይ የጫኑ ግለሰቦች የቫይረሱ ተጠቂ ሆነው የተገኙ ሲሆን፤ እነዚህም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኤርትራ፣ ካናዳና ጀርመንን ጨምሮ በሃያ ሃገራት ያሉ ኢትዮጰያውያን መሆናቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስለላውን ያከናወነው ከሃገር ቤትና መሠረቱን እስራኤል ካደረገ የሳይበር ደህንነት ኩባንያ ጋር በትብብር በመሆን እንደሆነም ታውቋል። 'ሳይበርቢት' የተሰኘው የእስራኤል ኩባንያው 'ኤልቢት ሲስተምስ' የተባለ ድርጅት አካል መሆኑም ተዘግቧል።

በስለላው ተጠቂ የሆኑ ግለሰቦች በኮምፒውተራቸው የሚያከናውኗቸውን ማንኛውም ዓይነት ተግባራትን የኢትዮጵያ መንግሥት መከታተል የሚችል ሲሆን ከዚህ አልፎም የኮምፒውተሩን ካሜራ በመጠቀም ቀጥታ ስለላ እንደሚያደርግም ድርጅቱ አጋልጧል።

ቴክኖሎጂው ወንጀልን በተለይ ደግሞ ሽብርተኝነት ለመከላከል ተብሎ የተፈበረከ እንደሆነ ታውቋል።

ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት መሰል ስለላዎችን ሲያከናውን ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን ደርጅቱ አስታውሷል።

ከዚህ በፊት ሂዩማን ራይትስ ዎችና 'ሲትዝን ላብ' የኢትዮጵያ መንግሥት ከጣልያን፣ እንግሊዝና ጀርመን ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስለላዎችን ማከናወኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ካዛኪስታን፣ ናይጄሪያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሩዋንዳ ቬትናምና ዛምቢያም መሰል ስለላዎችን በማከናወን ድርጊት ተኮንነዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ብቻ ሳይወሰን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎችንም እየሰለለ እንዳለ ያወሳው ሪፖርቱ ድርጊቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ሲል ይኮንናል።

የፖለቲካ መብት ተሟጋቾች የሚያደርጉትን የስልክ ንግግር በመቅረፅና በምርመራ ወቅት በመጠቀም እንደ አፍ ማዘጊያ እየተጠቀመው ነው ሲልም ይወቅሳል።

ምንም እንኳ መሰል ቴክኖሎጂ የሚያመርቱ ድርጅቶች ከመንግሥታት ጋር ሽብርተኝተን ለመዋጋት እንደሚሰሩ ቢታወቅም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን መሣሪያውን ተቃዋሚዎችን ለመስለል እየተጠቀመበት ነው፤ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪዎችን፣ እንዲሁም ተሟጋቾችን እያስፈራራበት ነው ባይ ነው ሪፖርቱ።

መንግሥት የግል ጋዜጦችን ከገበያው ገሸሽ ማድረጉን ተከትሎ ከ2010 ጀምሮ ቢያንስ 85 ጋዜጠኞች ሃገራቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ድርጅቱ ያትታል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የሲትዝን ላብን ጥናት አጣቅሶ ሳይበርቢት የተሰኘው ድርጅት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥና መሰል ድርጊቶች ሲፈፀሙ ቀጣዩ እርምጃ ምን እንደሆነ እንዲያሳውቅ መጠየቁን ዘግቧል።

ሳይበርቢት ቴክኖሎጂውን ለመንግሥታት ብቻ የሚሸጥ ሲሆን ሽያጩን ሲፈፀም ከሚመለከተው ከፍተኛ የመንግሥት አካል ፊርማ እንደሚጠይቅም አስታውቋል።

ሳይበርቢት በጉዳዩ ዙሪያ እንዲሰጥ ለተጠቀው አስተያየት ምላሽ ሲሰጥ ድርጊቱ መፈፀም አለመፈፀሙን አለማረጋገጡን አስታውቆ አስፈላጊውን ምርመራና እርምጃ ለመውሰድ ግን ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። እርምጃው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውሉን እስከሟቋረጥና ድርጊቱ ከተፈፀመ ደግሞ በይፋ ለሕዝብ ማሳወቅን ሊያካትት እንደሚችል ጠቁሟል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች እስራኤልን የመሰሉ ሃገራት ድርጅቶቻቸው መሰል ቴክኖሎጂዎችን ለሃገራት ሲሸጥ አስፈላጊው ምርመራ እንዲካሄድ በተለይ ደግሞ የሰብዓዊ መበት ጥሰት አለመፈፀሙን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይጠቁማል።

"የእስራኤል መንግሥት እያወቀ ሳይበርቢት የተሰኘው ኩባንያ ኢትዮጵያን ለመሰሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሚያከናውኑ ሃገራት ቴክኖሎጂውን ሲሸጥ ዝም ካለ እጅግ አደገኛ ነው" ሲሉ ሲንቲያ ዎንግ ይደመድማሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ