በላይቤሪያ ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንዲካሄድ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ

ጆርጅ ዊሃ እና ጆሴፍ ቦአካይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters/EPA

የምስሉ መግለጫ,

ጆርጅ ዊሃ እና ጆሴፍ ቦአካይ

በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር የተደረገው ምርጫ ላይ ማጭበርበር ነበር በሚል የቀረበው ማስረጃ በቂ ባለመሆኑ የምርጫው ሁለተኛ ዙር እንዲቀጥል የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህ ማለት ደግሞ በመጀመሪያው የምርጫ ውጤት እየመሩ ያሉት የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጆሴፍ ቦአካይ መካከል የሁለተኛ ዙር መለያ ምርጫ ይኖራል።

ይህ መለያ ምርጫ የዘገየ ሲሆን አሁን ግን የምርጫ ኮሚሽኑ የሚካሄድበትን ቀን ይቆርጣል።

በምርጫው ሦስተኛ የወጡትና የሊበርቲ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ቻርልስ በሩሚስኪን የምርጫውን ውጤት ተቃውመው ነበር።

ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ለመተካት የተደረገው ምርጫ ሁለተኛ ዙር መጀመሪያ ሊካሄድ የታሰበው እንደፈረንጆቹ ህዳር ሰባት ነበር።

በላይቤሪያ ላለፉት ሰባ ሦስት ዓመታት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ታይቶ አይታወቅም።

ኤለን ሰርሊፍ ስልጣን የያዙት እንደ አውሮፓውያኑ 2006 ላይ ሲሆን፤ ይህም የሆነው የእሳቸው ቀዳሚ ቻርልስ ቴለር በ2003 በአማፅያን ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ።

በቻርልስ ቴለር ጊዜ ላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ቴይለር ደግሞ በአሁኑ ወቅት በጎረቤት ሴራሊዮን ግጭት ለተፈፀመ የጦር ወንጀል ተጠያቂ በመሆን ሀምሳ ዓመት ተፈረዶባቸው በእንግሊዝ እስር ላይ ይገኛሉ።