በጨለንቆ 15 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

ግጭቱ የተከሰተበት ጨለንቆ አካባቢ Image copyright Google Maps

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ጨለንቆ ከተማ የመከላከያ ሰራዊት ሰዎችን እንደገደለ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።

በግድያው 15 ሰዎች ሲሞቱ 14 ሰዎች እንደቆሰሉም በፅሁፋቸው አስቀምጠዋል።

የሟቾቹን ቁጥር ከዚያ በላይ እንደሆነ የአካቢቢው ሰዎች ለተለያዩ መገናኛ ብዙሐን እየገለፁ ነው።

ጥቃቱ የደረሰው ሜታ ወረዳ ድንበር አካባቢ በምትገኝ የሳርካማ ቀበሌ ውስጥ አህመዲን አህመድ አሰሳ የተባለ ግለሰብ በሶማሌ ልዩ ፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ላይ መሆኑንም አቶ አዲሱ ጨምረው ፅፈዋል።

ጥቃቱን የሚያጣራ ከጨፌ ኦሮሚያ የተዋቀረ ኮሚቴ ወደ ቦታው እንደተላከ አቶ አዲሱ በፅሁፋቸው ገልፀዋል።

"የክልሉ መንግሥት ይህንን ጥቃት ፈፅሞ ያወግዛል"በማለት በፌስቡክ ገፃቸው ፅፈዋል።

"ቢያንስ 15 ሰዎች ተገድለዋል" በማለት የጨለንቆ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሱፊያን ኡስማን በስልክ ለ ቢቢሲ ገልፀዋል።

የተገደሉትንም ሰዎች ለመቅበር እየሄዱ መሆናቸውን አቶ ሱፊያን ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች