ሴቶች ዝቅ ብለው እንዲኖሩ የሚያስተምረው ትምህርት ቤት

ከቪዲዮ ላይ የተወሰደ የተማሪዎች ፎቶ Image copyright Pear Video

በሰሜን ቻይና ፉሸን በምትባል ከተማ የሚገኝ አንድ የባህል ማዕከል ሴቶችን፤ ሥራና ሴትነት አብሮ እንደማይሄድና ሁለቱን አንድ ላይ ለማስኬድ መሞከርም ለአዕምሮ ከባድ እንደሆነ እንደሚያስተምር ተደረሰበት።

የአስተምህሮቱ ዋና ዋና ይዘቶች እንደወንድ ወጥተው የሚሰሩ ሴቶች መጨረሻቸው አያምርም፣ ሴቶች የማህበረሰቡ መጨረሻ መሆን እንጂ ከፍ ለማለት መሞከር እንደሌለባቸው፤ እንዲሁም ሴቶች የአባቶቻቸውን፣ የባሎቻቸውንና የወንድ ልጆቻቸውን ትዕዛዝ መቀበል እንዳለባቸው የሚገልፁ ናቸው።

በተጨማሪም ሴቶች ባሎቻቸው ሲደበድቧቸው ወይም ሲጮሁባቸው መመለስ እንደሌለባቸውና አንዲት ሴት ከሦስት ከሚበልጡ ወንዶች ጋር ወሲብ ከፈፀመች ልትታመምና ልትሞት ትችላለች ብለውም ይመክራሉ።

ይህ ማዕከል ስለሚያስተምረው ጉዳይ ዜናው ይፋ በወጣበት ጊዜ የአገሪቱ መላ ህዝብን እጅጉን አስቆጥቷል። መንግሥትም ማዕከሉን በመዝጋት አፋጣኝ እርምጃ ወስዷል።

ህዝቡ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረ ገፆች ያደገረው ግፊት የቻይና ትምህርት ሚኒስቴር "የማዕከሉ አስተምህሮ ማህበራዊ እሴቶቻችንን የሚፃረር ነው" በማለት እርምጃ እንዲወስድ አስገድዶታል።

የ17 ዓመቷ ጂንግ አንድ ጊዜ ትምህርት ቤቱ ገብታ ነበር። በተወሰደው እርመጃ ደስተኛ መሆኗን ለቢቢሲ ገልፃለች።

የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለች ረባሽ ነች ብላ በማመን እናቷ ባህላዊ ትምህርቱ አደብ እንድትገዛ ያደርጋታል በማለት ወደ ትምህርተ ቤቱ ትልካታለች።

የጂንግ እናት ወደ መሰል የባህል ትምህርት ልጆቻቸውን እንደሚልኩ ቤተሰቦች በገጠር ያደገችና ብዙም ያልተማረች ነች።

"የትምህርቱ አካል ነው ተብሎ፤ ካለጓንት በእጄ ሽንት ቤት አፀዳ ነበር" በማለት ያሳለፈችውን ስቃይ ታስታውሳለች።

በቆይታዋም ይህን ሴቶች ሊያደርጉት እንደሚገባና የተፈጠሩትም ወንዶችን ለማገልገል እንደሆነ ተምራለች። ጂንግ እስካሁንም ለምን ጓንት እንዳልተሰጣትና እንደዚያ እንድትሰቃይ እንደተፈለገ አይገባትም።

ሌላው የማስተማሪያ ዘይቤ ሴቶቹ ጥፋት የሚሉትን እንዲናዘዙ ማድረግ ነው። ጂነግ እንደምትለው የትምህርት ቤቱ ሥርዓተ-ትምህርት በጥንት አስተምህሮቶች እንዲሁም የቤት ውስጥ ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑን ትናገራለች።

አስተምህሮቱ ማንኛዋም ጤነኛ ሴት የምትቋቋመው አይደለም። "እኔም ሰባት ቀን መቆየት ሲኖርብኝ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ የትምህርት ቤቱን የብረት አጥር ዘልዬ ወጣሁ"ትላለች።

ጂንግ እንደምትለው እንደ ቤጂንግና ሻንጋይ ባሉ ከተማዎች የሚኖሩ የተማሩ ሴቶች የዚህን ትምህርት ቤት ዜና ሲሰሙ እጅግ ሊደነግጡ ይችላሉ።

Image copyright Pear Video

ነገር ግን እነዚህ ዘመን ያለፈባቸው የትምህርት ቤቱ አስተምህሮቶች በገጠር አካባቢዎች በተለይም በቻይና ትንንሸ ከተሞች እንዳሉ ናቸው።

ለብዙ ሺህ ዓመታት በነበረው የቻይና ፊውዳል ሥርዓት እንዲህ ዓይነቱ የሴቶች ባህሪ በጣም አስፈላጊ የሚባል ነበር። ይህ ማለት ደግሞ የአባትን ትእዛዝ ማክበር፣ ክብረ ንፅህናን መጠበቅና ከዕውቀት ነፃ ሴት መሆን ከሴቶች የሚጠበቅ ነበር።

እነዚህ ነገሮችን ሴቶች በቤትና በትምህርት ቤት እንዲማሩት ይደረግ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ሴቶችን ለመጨቆንና ለመርገጥ አስችሏል።

ማኦ "ሴቶች የሰማይን ግማሽ የያዙ ናቸው" በማለት ነገሮችን እስኪለውጡ ድረስ ሴቶች በጭቆና ስር ነበር የሚኖሩት። ከዚያ በኋላ ግን ሴቶች በማህባራዊ ህይወት ደረጃቸው እየተሻሻለ መጥቷል።

ቢሆንም ግን በባህላዊ ትምህርት ስም ሴትን የሚጨቁኑ የፊውዳል ሥርዓት እሴቶች ተመልሰው ሊመጡ ነው የሚል ስጋት እየተፈጠረ ነው።

ገንዘብ መሰብሰብ

የፉሸን ዓይነቱ ትምህርት ቤት አላማ ፖለቲካ ሳይሆን ገንዘብ ነው። ትምህርት ቤቱ ለማስተማር ፍቃድ የሌለው ቢሆንም እያስከፈለ ያስተምራል። መስራቾቹ በተለያዩ የቻይና ከተሞች ትምህርት ቤትና ማዕከሎችን በመክፈት ሲነቀሳቀሱ ቆይተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ትምህርት ቤቱ ሲዘጋ 10ሺህ ተማሪዎች ነበሩት። ትምህርት ቤቱን ያቋቋመው ኢንተርፕራይዝ የተቋቋመው ግን በተማሪዎች ልገሳ ነው። ኢንተርፕራይዙ ጎን ለጎን የሚያካሂደው ሌላ ንግድም አለው።

ትምህርት ቤቱ አስቸጋሪ ልጆች ያላቸውን ቤተሰቦች ኢላማ ያደርጋል። ኩባንያዎችንም ጥሩ የሥራ ግንኙነት እንዲፈጠር እናደርጋለን በማለት ይቀርባል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2014 ላይ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረ ሌላ ማዕከል ተዘግቷል።

Image copyright Pear Video

እንደእነዚህ ያሉ ተቋማት ባህላዊ ትምህርትን በማስፋፋት ስም ትርፍ እየሰበሰቡ በመሆኑ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው። ቢሆንም ግን አሁንም እየተንቀሳቀሱ ያሉት በርካታ ናቸው።

የፉሸን ዋናው ማዕከል ቢዘጋም አሁንም በሌሎች ከተሞች ያሉ ቅርንጫፎቹ እየሰሩ ነው።

የዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ለምን ገበያ ኖራቸው? ብዙዎቹ ተማሪዎች ያልተማሩ የገጠር ሴቶች፣ በትዳራቸው ደስተኛ ያልሆኑና በባሎቻቸው የሚጨቆኑ ናቸው።

ስለዚህም ወደ ትምህርት ቤቱ ሄደው እንደእነሱ ያሉ ሴቶችን ማግኘት ያስደስታቸዋል። አጋር ያገኙም ይመስላቸዋል።

መገናኘታቸውንና ሀሳብ መለዋወጣቸውን በመውደድ ሴቶቹ በመጨረሻ የትምህርት ቤቱ በጎ ፍቃድ አገልጋይ ይሆናሉ።

አንድ የገጠር ሴቶች ላይ የሚያተኩር ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነችው ዚ ሉሃ፤ የዚህ ዓይነቱን ችግር ሴቶችን እንዲማሩ፣ ማህበራዊ ድጋፍ እንዲኖራቸውና የህግ ከለላ እንዲያገኙ በማድረግ ለመፍታት ትክክለኛው መንገድ እንደሆነ ትናገራለች።

ይህ ካልሆነ ግን የገጠር ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ፆታዊ ጥቃት እና የመሬት ባለቤት መሆን ያለመቻል ችግር መቼም እንደማይፈታ ትጠቁማለች።

ነገር ግን "ታሪክ በአንዴ አይለወጥም። እነዚህ ሴቶች ዝቅ እንዲሉ ለሚያስተምሩ ማዕከሎች ትልቅ ቦታ መስጠት አያስፈልግም። ይልቁንም ቀልደው የሚያልፏቸው ዓይነት ናቸው። የቻይና ህዝብ የሴቶችን እኩልነት እየተቀበለ መጥቷል'' ትላለች።

ተያያዥ ርዕሶች