የመንግሥት መግለጫ አልዘገየም?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ Image copyright ASHRAF SHAZLY

በአገሪቱ ያለውን ግጭትና አለመረጋጋት በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እሁድ ምሽት በሰጡት መግለጫ ግጭትና አለመረጋጋቱ የአገሪቱን ሰላም ማወክ ደረጃ ላይ መድረሱን በማመን መንግሥትም የግጭቶቹን መሰረታዊ ችግር በመለየት የማያዳግም መፍትሄ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የፌደራል መንግሥት በተለይም ከፍተኛ ግጭቶች ከተከሰቱባቸው ከኦሮሚያና ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ጋር ችግሩን አስመልክቶ በመስራትና ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ሳለ፤ ግጭቱ አገርሽቶ በምዕራብ ሐረርጌ በዳሮለቡ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ ንፁህ የሶማሌ ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ ንብረትም መውደሙን ገልፀዋል።

መንግሥት ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረሃይል ማቋቋሙንና ማጣራቱን ተከትሎ እርምጃ እንደሚወስድ፤ የሂደቱንም ዝርዝር ለህዝብ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ብዙዎች ህይወታቸውን እንዳጡ፣ ብዙዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉና እንዲሁም ሃብትና ንብረት መውደሙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ በጨለንቆና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ ማጋጠሙንም አስታውቀዋል።

ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላምን ያሰፍኑ ዘንድ መንግሥተ የፀጥታ ኃይሎችን ማሰማራቱንና በፀጥታ ሃይሎች ተልዕኮ ላይ የጨለንቆን ግጭት ጨምሮ ክፍተቶች የሚታዩ ከሆነ መንግሥት ነገሮችን እንደሚያጣራ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በሚገኙት የአዲግራት፣ ወለጋ፣ አምቦ፣ ደብረ ታቦር፣ ወልድያ፣ ባህርዳርና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ህይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱንና ንብረት መውደሙን አስታውቀዋል።

የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ምክንያታዊ አስተሳሰብን ተከትለው ከግጭት በመራቅ ለሐገራቸው ተስፋ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ነገሮች እስኪረጋጉና የተማሪዎች ስጋት እስኪቀረፍ በዩኒቨርሲቲዎች የሰዓት እላፊ ተጥሏል። በዚህም መሰረት የተቋማቱ የሰዓት እላፊ ገደብ የፀጥታ ኃይሎች በቅጥር ግቢዎቹ መረጋጋት እንዲያሰፍኑ መደረጉን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙሃንን በማስጠንቀቅ የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ይህን ተላልፎ የሚገኝ የህዝብም ሆነ የግል ሚዲያ ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

በንግግራቸው በተደጋጋሚ መንግሥት ከግጭቶቹ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚደርስበትን ነገር ለህዝብ እንደሚያሳውቅ መግለፃቸው፤ ምናልባትም በእያንዳንዱ ደረጃ ያለውን ነገር ለህዝብ ማሳወቅ ችግሩን እንዳይባባስ የማድረግ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን የተረዳው ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ የሚገልፁ አሉ።

ተያያዥ ርዕሶች