ኤኤንሲ ሲሪል ራማፖሳን የፓርቲው መሪ አድርጎ መረጠ

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሲሪል ራማፎዛ

የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የአፍሪካዊያን ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ሲሪል ራማፖሳ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን ተክተው የፓርቲው መሪ እንዲሆኑ መረጠ።

የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ራማፖሳ የቀድሞዋን የጃኮብ ዙማን ባለቤት እና ሚኒስትር የነበሩትን ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን ከተራዘመ የምርጫ ሂደት በኋላ በማሸነፍ ነበር የተመረጡት።

ራማፖሳ የፓርቲውን መሪነት ሲይዙ በአውሮፓውያኑ 2019 በሚደረገው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መሪ ሆነው ለመመረጥ ሰፊ ዕድልን ይሰጣቸዋል።

የፓርቲውን መሪነት ለመያዝ የተደረገው ከባድ ፉክክር ጠንካራ ፖለቲካዊ ሽኩቻ በማስከተሉ፤ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ኤኤንሲ ለሁለት ሊከፈል ይችላል የሚል ስጋትን ፈሯል።

የፓርቲው ቃል-አቀባይ እንዳሳወቁት ሲሪል ራማፖሳ ድላሚኒ ዙማን 2440 ለ 2261 በሆነ ድምፅ በማሸነፍ ነው ለመሪነት የተመረጡት።

የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ በምርጫው የተሳተፉ የፓርቲው ተወካዮችና የጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን ጎዳና ላይ ሲገልፁ ነበር።

የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የድላሚኒ ዙማ ደጋፊዎች የድምፅ ቆጠራው በድጋሚ እንዲካሄድ በመጠየቃቸው የምርጫው ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ዘግይቶ ነበር።

የምርጫው ሂደት ዕሁድ ዕለት ነበር የጀመረው።

ራማፖሳ ማን ናቸው?

*በአውሮፓውያኑ 1952 ሶዌቶ፤ ጆሃንስበርግ ውስጥ ተወለዱ

*በፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት በ1974 እና 76 ታሰሩ

*በ1982 የማዕድን ማውጫ ሰራተኞች ማህበርን መሰረቱ

*ኔልሰን ማንዴላ ከዕስር ሲፈቱ የሥነ-ሥርዓቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ነበሩ

*በ1994 የሃገሪቱ ምክር ቤት አባልና የሕገ-መንግሥት ጉባኤ ሰብሳቢ ሆኑ

*በ1997 ሙሉ ለሙሉ ወደ ንግድ ፊታቸውን አዙረው በደቡብ አፍሪካ ካሉ ሃብታሞች አንዱ ለመሆን በቁ

*በ2014 የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኑ

*አሁን የኤኤንሲ መሪ እንዲሆኑ ተመረጡ