ሸማቹ በውጭ ምንዛሪ ለውጡ ማግስት

Market-Ethiopia

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER

የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ከተደረገ ሁለት ወራት አልፈዋል። ይህም በብዙዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ አሳደረ? መንግሥትስ በወሰደው እርምጃ ያሰበውን ውጤት ማስመዝገብ የሚችልበት አቅጣጫ ላይ ነው ወይ? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲነሱ ግድ ይላል።

ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው አዲስ አበቤዎች ባለው የኑሮ ውድነት ላይ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ መደረጉ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን በእጅጉ እንዳከበደው ገልፀዋል።

ወ/ሮ አስቴር ገብሩ እንደሚሉት ከዶላር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው እቃዎችን ጨምሮ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ሳይቀር ጭማሪ ታይቷል።

የሚጠቀሙት ባለ አንድ ሊትር ዘይትን በ52 ብር ነበር የሚገዙት። የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ በተደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ግን ዘይቱ የስምንት ብር ጭማሪ አሳይቷል። በተመሳሳይ የሳሙና ዋጋ እጅጉን መጨመሩን በምሬት ይገልፃሉ።

ድንገት በሚገዟቸው ሸቀጦች ላይ በተደረገው ጭማሪ ምክንያት ወ/ሮ አስቴር ከባለሱቅ ደንበኞቻቸው ጋር በተደጋጋሚ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት ቸርቻሪ ደንበኞቻቸው ለዋጋ ጭማሪው የሚሰጡት ምክንያት የተደረገው የዶላር ምንዛሬ መጨመርን ተከትሎ ጅምላ አከፋፋዮች ዋጋ መጨመራቸውን ነው።

ጅምላ ሻጮች በበኩላቸው ደግሞ አስመጪዎች ዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው የሚያከፋፈሉበት ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ጅምላ አከፋፋዮች አንዱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ጅምላ አከፋፋዮች በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርገው እያከፋፈሉ መሆናቸውን አምነው ለዚህም ምክንያቱ አስመጪዎች ያደረጉት የዋጋ ጭማሪ መሆኑን እንደምክንያት ይተቅሳሉ።

እንደማስረጃም ከአንድ አስመጪ ጋር ከሁለት ወራት በፊት የነበራቸውን ውል አሳይተውናል። ይህ አስመጪ ኩባንያ ከጅምላ አከፋፋይ ድርጅታቸው ጋር አንድ ፍሬ የጠረጴዛ ናብኪን በ12 ብር ሊያቀርብላቸው ተስማምቶ ነበር። ከ10 ቀናት በኋላ ግን የዶላር መጨመርንና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እንደ ምክንያት ጠቅሶ በጻፈው ደብዳቤ ዋጋውን 14.50 ብር አድርሶታል።

ያለቀላቸውን ምርቶች ከውጭ ከሚያስገቡ ኩባንያዎች አንዱ የሌግዠሪ እና ፖፑላር ትሬዲንግ ነው። የኩባንያው ማርኬቲንግ ሃላፊ አቶ አቤል አለባቸው ለዋጋ ጭማሪው ዋናው ምክንያት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው ይላሉ። አቶ አቤል እንደሚሉት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በጣም ከባድ ስለሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ምርቶችን በፍጥነት ማስገባት አዳጋች እንደሆነ ያስረዳሉ።

''ለምሳሌ ሳሙና እናስመጣለን፤ ምርቱ በገበያ ላይ ምንም ያህል ተፈላጊ ቢሆንም በመጋዝን ውስጥ ያለንን በሙሉ በአንድ ግዜ አውጥተን አንሸጥም። ምክንያቱም በአጭር ግዜ ውስጥ ዶላር አግኝቶ ምርቱን እንደገና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ስለማንችል ከማርኬቲንግ ስትራቴጂ አንጻር ምርታችን ከገብያ ጠፍቶ እንዳይረሳ በአንስተኛ መጠን ወደ ገብያ እናወጣዋለን'' ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ አይነት አካሄድ ደግሞ በገበያ ላይ የምርት እጥረት በመፍጠር የሸቀጦች ዋጋ ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሳሙኤል ሳህሌ ናቸው።

አቶ ሳሙኤል መንግስት የብር የመግዛት አቅምን የቀነሰው የወጪ ንግድን ለማቀላጠፍ በማሰብ እንደሆነና የዚህ ውሳኔ የመጨረሻ ግብም ወደ ውጪ የሚላከው ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ከምናስገባው ምርት ጋር መጣጣም እንዲችል ማድረግ መሆኑን ይገልፃሉ።

መንግሥት በወሰደው እርምጃ አዎንታዊ ለውጦችን መመልከት ተችሏል? የሚለው ደግሞ ሌላው ጥያቄ ነው።

አቶ ሳሙኤል ''ሀገሪቱ ከምትገኝበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንጻር መንግሥት የወሰደው እርምጃ ትክክለኛ ነው ብዬ አላምንም'' ይላሉ። ሆኖም ግን የመንግሥት ውሳኔ ውጤታማ ነው ወይም አይደለም ለማለት ጊዜው ገና መሆኑንና ቢያንስ ሦስት ወራት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

በንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የገበያ መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኢቲሳ ደሜ በበኩላቸው አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ወደፊት ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ብቻ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን፤ በዚህም የዋጋ ጭማሪዎች መታየቱን ይናገራሉ።

እስከ 120 በመቶ አግባብ ያልሆነ ጨማሪ ያደረጉ ስምንት አስመጪዎች እና አከፋፋዮች መከሰሳቸውንም ጠቁመዋል። እንዲሁም ሌሎች በርካታ ድርጅቶችንም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ወደ ህግ ለማቅረብ አስፈላጊ መረጃዎችን እያሰባሰቡ መሆኑን አቶ ኢቲሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አላግባብ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችን ተጠያቂ የማድረጉ እርምጃ እንዳለ ሆኖ፤ የሸማቹን የዕለት ከዕለት ኑሮ ያከበደና ትከሻውን ያጎበጠውን ገበያ ለማረጋጋትስ የመንግሥት እጅ ከምን? የሚለው ጥያቄም ከምንም በላይ ምላሽ የሚሻ መሆኑን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ተናግረዋል።