ከስራ አጥነት ወደ ራስን ቀጣሪነት

ጓደኛሞቹ ቢታንያ ብስራት እና ዮናታን ከበደ
የምስሉ መግለጫ,

ዮናታን ከበደ እና ቢታንያ ብስራት

ቢታንያ ብስራት እና ዮናታን ከበደ ጓደኝነታቸው የሚጀምረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆርናሊዝም እና ኮሚኒኬሽን ተማሪ ሳሉ ነው። ቢታንያ እና ዮናታን ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከወጡ በኋላ በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ተሰማርተው ለመስራት ፍላጎቱ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ጓደኛሞቹ እንደሚሉት ያለመታከት ሥራ ቢፈልጉም ለሁለት ዓመታት ያክል ሥራ-አጥ ተብለው መቆየታቸው እንደሚያስቆጫቸው ይናገራሉ።

እነሱ እንደሚሉት ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ ከሁለት ዓመታት በኋላ አንድ የንግድ ሃሳብ መጣላቸው። ቢታንያ ሲያስረዳ፤ ''የንግድ ሃሳባችን በሀገራችን ብዙም ያልተለመደ ነው። ይህም ሰዎች ካሉበት ሆነው አንድን ቁስ ገዝተን እንድናቀርብላቸው ወይም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንድንወስድ በስልክ ያዙናል እኛም የማጓጓዣ ወጪውን በማስከፈል ትዕዛዙን በፍጥነት እንፈጽማለን'' ይላል።

አሁን ለምሳሌ አንድ ሰው በተጣበበ የሥራ ሰዓት ላይ ከሆኑ ወይም ወደ ምግብ ቤት ሄደው መመገብ ካልፈለጉ፣ ትዕዛዛቸውን በስልክ ተቀብለን የሚፈልጉትን ምግብ ከሚፈልጉበት ምግብ ቤት እናቀርብላቸዋለን። ይህም አንድ ሰው ሆቴል ድረስ ሄዶ እሰኪመለስ ያለውን ጊዜ እንዲሁም ምግቡ ተሰርቶ እሰከሚቀርብ የሚባክነውን የደንበኛችንን ጊዜ መቆጠብ ያስችላል ሲል ዮናታን ይናገራል።

ቢታንያ እና ዮናታን ይህን የቤት ለቤት የተለያዩ ቁሶችን የማቅረብ ሥራ የጀመሩት ዳማስ የምትባል አነስተኛ መኪና እና ሞተርሳይክል በመጠቀም ነው።

ቢታንያ እና ዮናታን አንደሚሉት እንጀራን ለሆቴሎች ከሚያቀርብ ድርጅት ጋር ባላቸው ስምምነት መሰረት የእለት ሥራቸውን የሚጀምሩት እንጀራ ለተለያዩ ሆቴሎች በማደረስ ነው። ከዚያ በኋላ ቦሌ አካባቢ ቆመው ሌሎች የሚመጡ ሥራዎችን ይጠባበቃሉ። ቦሌ አካባቢ ጥቂት ደንበኞች አሉን እነሱም የተለያዩ ሸቀጦችን እና ፋይሎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንድንውስድ ይጠይቁናል፤ እኛም በደስታ ስራውን ተቀብለን እንሰራለን ይላሉ።

ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን መኪና እና ሞተር ሳይክል ለመግዛት እንዲሁም ሥራውን ለመጀመር 150ሺ ብር አስፈልጓቸው እንደነበር ይናገራሉ። ''ከአበዳሪ ተቋማት ባገኘነው ብድር እና ከቤተሰብ ከተሰጠን አነስተኛ የገንዘብ ስጦታ መኪናዋን በ120 ሺ ብር ገዛናት። መኪናዋን ከበድ ላሉ እቃዎች እንጠቀማታለን ሞተሩን ደግሞ ቀለል ላሉ እቃዎች በፍጥነት ለማድረስ እየተጠቀምንበት እንገኛለን'' ሲል ዮናታን ይናገራል።

የተሰማራንት የሥራ መስክ የተለመደ አይደለም። ሥራችንን ለማስተዋወቅ በራሪ ወረቀቶችን እንበትናለን። እኛ ከምንሰራው የማስታወቂያ ሥራ በላይ ደግሞ በአገልግሎታችን የረኩ ሰዎች ስለ ሥራችን መልካም ነገር ለሌሎች ሲነግሩ የተሻለ እንደሆነ ስለምናውቅ ለሁሉም ደንበኞቻችን ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንጠራለን ሲል ቢታንያ ያስረዳል።

ሁለቱ ጓደኛሞች ስለ ቅርብ ጊዜ እቅዳቸው ሲናገሩ፤ ''ከደንበኞቻችን በቀረበልን ጥያቄ መሰረት ግዜ ለሌላቸው ሰዎች የሸቀጦችን ዝርዝር በመቀበል ከሱፐርማርኬቶች አስቤዛ በማድረግ እቤት ድረስ እንወስዳለን በዚህም የብዙዎችን ውድ ግዜ ማደን እንችላለን'' ሲሉ ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓት ስራቸው ብዙም እንዳልተለመደ የሚናገሩት ጓደኛሞቹ ወደ ፊት ግን ብዙ ፈላጊ እንደሚኖረው ባለሙሉ ተስፋ ናቸው።