ቻይና ባሕር ላይ የሚያርፍ ግዙፍ አውሮፕላን ሞከረች

ኤጂ600 አውሮፕላን Image copyright AFP

ቻይና በዓለም ላይ ግዙፍ በመሬትና በውሃ ላይ ማረፍ የሚችል አውሮፕላን ሰርታ የተሳካ የአንድ ሰዓት የሙከራ በረራ አደረገ።

የደቡባዊ ቻይና ግዛት ከሆነችው የጓንግዶንግ ዡሃይ አየር ማረፊያ ተነስቶ የሙከራ በረራውን ያደረገው ይህ በውሃ ላይም ማረፍ የሚችል አውሮፕላን ቦይንግ 737ን የሚያክል ሲሆን ባለአራት ሞተር ነው።

አውሮፕላኑ እስከ 50 የሚደርሱ ሰዎችን አሳፍሮ በአየር ላይ ለ12 ሰዓታት ሊቆይ ይችላል።

ይህ አውሮፕላን በእሳት አደጋ ወቅትና በባህር ላይ በሚያጋጥሙ አደጋዎች ነፍስ የማዳን ተግባራት ላይ መሰማራት ከመቻሉም በላይ ለወታደራዊ አገልግሎት ሊውል ይችላል።

በተለይ በአወዛጋቢው የደቡብ ቻይና ባሕር አካባቢ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ተነግሯል።

ይህ ኤጂ600 በመለያ ስም ኩንሎንግ የተባለው አውሮፕላን ቻይና የእኔ ናቸው ወደምትላቸው ደቡባዊ የባሕር ግዛቶች ድረስ የመጓዝ አቅም አለው።

የቻይና መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ዥንዋ አውሮፕላኑን ''የባሕር ጠረፍንና ደሴቶችን የሚጠብቅ መንፈስ'' ሲል ገልፆታል።

አውሮፕላኑ ሲነሳ በሀገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ተላልፏል፤ ሲያርፍም በሰንደቅ ዓላማና በወታደራዊ ሙዚቃዎች በታጀቡ ዜጎች አቀባበልተደርጎለታል።

የግንባታው ሂደት 8 ዓመታትን የፈጀው ይህ አውሮፕላን መሸከም የሚችለው ከፍተኛ ክብደት 53.5 ቶን ያህል ነው።

ከአንዱ ክንፍ እስከሌላኛው ደግሞ 38.8 ሜትር ይረዝማል። በቻይና ብቻ እስካሁን 17 የግዢ ጥያቄዎች መቅረባቸውም ተዘግቧል።

ከዚህ አውሮፕላን ቀደም ብሎ የተሰራው በራሪው ጀልባ በመጠን ከፍ ያለ ነበር። ስፕራውስ ጉዝ ወይንም ደግሞ በቴክኒክ ስያሜው ሁግስ ኤች-4 ሔርኩልስ 97.54 የሚረዝም ክንፍ ነበረው።

ምንም እንኳ በ1947 ለ26 ሰከንድ ብቻ የቆየ በረራ አንዴ አድርጎ ቆሟል። በአሁኑ ወቅትም በኦሪገን ሙዚየም ተቀምጦ ይጎበኛል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለአሜሪካ ጦር መጓጓዣ እንዲሆን ተብሎ የተሰራ ሲሆን የክንፎቹ ርዝማኔ 61 ሜትሮች ያህል ነበር።