የቱኒዚያ ተጓዦች የተጉላሉት በሽብር ስጋት ነው

A women are seen in front of the Dubai airline Emirates office, at Tunis-Carthage International Airport in Tunis, Tunisia, December 25, 2017

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቱኒዚያና በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ መካከል የተፈጠረው ውጥረት የሽብር አደጋ ስጋት ነው ስትል ቱኒዚያ አስታውቃለች።

አርብ ዕለት ነበር የቱኒዚያ ዜግነት ያላቸው ሴቶች ኤሚሬትስ አየር መንገድን ተጠቅመው ሊያደርጉት የነበረው በረራ ለምርመራ በሚል ምክንያት እንዲስተጓጎል የተደረገው።

በምላሹ ቱኒዚያ ኤሚሬትስ አየር መንገድ በመዲናዋ ቱኒዝ እንዳያርፍ አግዳለች።

አንድ የቱኒዚያ ባለሥልጣን እንዳሳወቁት የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ባለሥልጣናት "በቱኒዚያ ሴቶች የሽብር ጥቃት ሊፈፀም" እንደሚችል መረጃው ደርሷቸዋል።

የቱኒዚያ ፕሬዚደንት ቃል-አቀባይ የሆኑት ሰዒዳ ጋራሽ እንደተናገሩት ኤሚሬትስ አየር መንገድ ቱኒዚያዊያን ሴቶች አየር መንገዱን ከመጠቀም ለተወሰነ ጊዜ ያህል እንዲያግድ ትዕዛዝ ደርሶታል።

ቃል -አቀባይዋ እንደተናገሩት "ከሶሪያና ኢራቅ የሚመለሱ የአይ ኤስ አባላት መካከል የቱኒዚያ ዜግነት ያላቸው ወይም የቱኒዚያን ፓስፖርት ተጠቅመው ሽብር ሊፈፅሙ እንደሚችሉ አየር መንገዱ መረጃው ስለደረሰው ነው እርምጃውን የወሰደው።"

"ምንም እንኳ የቱኒዚያ መንግሥት መረጃው የማይናቅ መሆኑን ቢረዳም ቱኒዚያውያን ሴቶች በአውሮፕላን ማረፊያዎች መንገላታታቸው ትክክል አይደለም" ሲሉም አክለዋል ሰዒዳ።

የቱኒዚያው ፕሬዝደንት በዢ ካይድ ኤስቤሲ በበኩላቸው "ምንም ይሁን ምንም የቱኒዚያ ሴቶች መብት ሊነካ አይገባም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ኤሚሬትስ አየር መንገድን ሲጠቀሙ የነበሩ ቱኒዚያውያን ሴቶች "በምን ምክንያት እንግልት ውስጥ ልንገባ እንደቻልን ማንም አላስረዱንም" ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

በዚህ ውጥረት መካከል ነበር የቱኒዚያ መንግሥት የተባበሩት ኤሜሬት ሃገራት ለሁኔታው አስፈላጊውን ማጣሪያ አካሂዶ ምላሽ እስካልሰጠ ድረስ ኤሚሬትስ አየር መንገድ በሃገሪቱ መዲና ቱኒዝ እንዳያርፍ ያገደችው።

የቱኒዚያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር እንዳሉት "አሁንም ቢሆን አስፈላጊው ማጣራት ተካሂዶ መፍትሄ እስካልተገኘ ድረስ እገዳው ተግባራዊ መሆኑን ይቀጥላል" ብለዋል።