ቻይናዊው የመብት ተሟጋች የስምንት ዓመት እሥር ተፈረደበት

ቻይናዊው የመብት ተሟጋች ዉ ጋን Image copyright YOU JINGYOU

ቻይናዊው የመብት ተሟጋች ዉ ጋን በ2015 ነበር በርካታ ቻይናውያን ለእሥር በተዳረጉበት ወቅት ተይዞ ወደ ወህኒ የወረደው።

ዉ በይነ-መረበን በመጠቀም ቻይናውያን ባለሥልጣናት የሚያደርጉትን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር በማጋለጥ ይታወቃል።

ዉ ላይ ብያኔውን ያሳለፈው ቲያንዢን ግዛት የሚገኘው ፍርድ ቤት "ባለው አገዛዝ ደስተኛ ባለመሆኑ ምክንያት የአንዲት ሉዓላዊት ሃገርን ሕልውና የሚገዳደር ተግባር ፈፅሟል" ብሏል።

ፍርድ ቤቱ አክሎም "ዉ በይነ-መረብን በመጠቀም ኢ-ተዓማኒ ዜናዎችን አሰራጭቷል፤ እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦችን ተሳድቧል" በማለት ወቅሶታል።

ዉ ጋን "የተፈረደበኝ ፍርድ ፍትሃዊ አይደለም" በማለት ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

ዉ ቻይና ውስጥ የባለስልጣናት ግፍ ተጠቂ ናቸው ያላቸውን ሰዎች ድርጊት በበይነ-መረብ በማጋለጥ ነው የሚታወቀው። ከእነዚህም አንዱ የሆነው አስገድዶ የደፈራትን የኮሚኒስት ፓርቲ አባል በፍራፍሬ መቁረጫ ቢላ ወግታ የገደለች ቻይናዊት ታሪክ አንዱ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ያለጥፋታችን በሰው መግደል ወንጀል ተጠያቂ ሆነናል የሚሉትን አራት ቻይናውያን ድምፅን በማስተጋባትም ይታወቃል።

Image copyright YOU JINGYOU

በአንድ ወቅት የሦስት ቻይናውያን ባለስልጣናትን ጭንቅላት የፎቶ አርትኦት ጥበብ (ፎቶሾፕ) በመጠቀም በሦስት አሳማዎች ጭንቅላት በመተካት "የዓለማችን በጣም ተፈላጊዎቹ ሦስት ወፍራም አሳማዎች" በማለት የለቀቀው ፎቶ በጣም መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበረ አይዘነጋም።

አራቱን ቻይናውያን በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የእሥር ቅጣት ያስተላለፉት ዳኛን ደግሞ እንደ ሂትለር ያለ ፂም በማድረግ "ለዚህ ፍርድ ምን ያህል ገንዘብ እንደተከፈልዎት ያጋልጡ" የሚል ፅሁፍ ያለበት መፈክር የያዘ ፎቶ አሰራጭቶ ነበር።

በ2015 የቻይና ክስተት ከ200 በላይ የህግ ሰዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መታሰራቸው አይዘነጋም።