ጠቅላይ ሚንስትሩ ተገደው እንዲቀርቡ ተጠየቀ

አቶ በቀለ ገርባ

የፎቶው ባለመብት, Bekele Gerba/Facebook

በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ በፍርድ ቤት ጥሪ የቀረበላቸው የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ፍርድቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

የመከላከያ ምስክር ሆነው ከተጠሩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ሥራ ስለሚበዛባቸው ፍርድ ቤት መቅረብ እንደማይችሉ የሚገልፅ ደብዳቤ ተልኳል።

የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን መቅረብ የማይችሉ ከሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲያዝላቸው በፍፁም አልችልም ማለት ግን ሕገ መንግስታዊ መሰረት እንደሌለው በመግለፅ ተከራክረዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ጠቅላይ ሚንስትሩ በፖሊስ ተገደው ፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸው ብለዋል።

አቶ ኃይለማርያም ጥሪ የቀረበላቸው እንደ ግለሰብ እንጂ እንደ መንግሥት ስላልሆነ ጽህፈት ቤታቸው ምላሽ መስጠት አይችልም ያሉት አቶ በቀለ፤ ለመገኘት ፈቃደኛ ካልሆኑ እንደማንኛውም ዜጋ ፖሊስ አስገድዶ ፍርድ ቤት ሊያቀርባቸው ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

የተከሳሾች መከላከያ ምስክሮች የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ አባዱላ ገመዳ በቀሪዎቹ ሁለት ቀናት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላም በኩል በዚሁ የክስ መዝገብ 12ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት አቶ ተስፋዬ ሊበን ቶሎሳ በተለያየ ጊዜያት በኤሌትሪክ ሽቦ በደረሰባቸው ግርፋት እና ሌሎች ስቃዮች ተገደው እንደ ማስረጃ የቀረበባቸው ሰነድ ላይ መፈረማቸውን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። የተከላካይ ጠበቃቸውም ይህንኑ አረጋግጧል።

ማክስኞ ጠዋት የተሰየመው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 4ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለከሰዓት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀርቷል።