ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አዲስ ሃሳብ አቀረበች

ሳሚ ሽኩሪ እና ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ
የምስሉ መግለጫ,

የግብፅ እና የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ ከኢትዮጵያው አቻቸው ከዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጠናከር ላይ የተነጋገሩ ሲሆን፤ ሹክሪ ቀላልና ተግባራዊ መሆን የሚችል ያሉትን ምክረ-ሃሳብ ኢትዮጵያ እንደምትመለከተው ዶክተር ወርቅነህ ገልፀዋል።

የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ሳሚ ሹክሪ፤ "ሉአላዊነትን፣ የጋራ መተማመንን መሰረት ያደረጉና ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተሉ ሥራዎች ተከናውነዋል" ብለዋል። ሆኖም ግን ላለፉት አስር ወራት ሲካሄዱ የቆዩት ውይይቶች በቂ ውጤት ማስገኘት አለመቻላቸውንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳዮች ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚፈጥረው ስጋት እንደማይኖር በመግለፅ "አለመግባባቶች ሲኖሩም ሕጋዊ አሰራሮችን በመከተል መፍታት ይቻላል። በሁለቱም ሃገራት የሚቆጣ ህዝብ አይኖርም። ኢትዮጵያም ግብፅን ለመጉዳት የምትሰራው ሥራም አይኖርም" ብለዋል።

96 በመቶ ህዝባቸው በረሃማ በሆነ አካባቢ እንደሚኖርና ህይወቱም በአባይ ወንዝ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያስታወሱት የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር "የግብፅ ህዝብ ተቆጥቷል ባልልም ስጋት ላይ መውደቁን ግን መናገር እችላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። ቢሆንም ግን የኢትዮጵያን የመልማት እንቅስቃሴ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።

ጉዳዩ የሁለቱ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ሱዳንንም እንደሚመለከት የገለፁት ሁለቱም ሚንስትሮች፤ በውይይትና በጋራ በመስራት መፍትሄ ለማምጣት እንደሚጥሩ ገልፀዋል። ፖለቲካዊ ሳይሆን ሳይንሳዊ ጥናቶችን መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንደሚበጅና ተቀባይነት እንደሚኖረውም ሳሚ ሹክሪ ተናግረዋል።

አዲሱ ምክረ-ሃሳብ የእስካሁኑን መጓተት ለማካካስና ቶሎ ወደ መፍትሄ ለመግባት የሚረዳ ቀላል፣ ከፖለቲካዊ እሳቤ የራቀና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መሆኑን ሹክሪ አስረድተዋል።

ጉዳዩን ለፖለቲካና ለመሪዎች ብቻ የሚተው አለመሆኑን በማስረዳት "ጥናቱን እንዲያካሂድ የሦስታችንንም ሃገራት ፍቃድና ተቀባይነትን ያገኘው ዓለም አቀፉ ተቋም፤ የሚደርስበትን ማንኛውንም ውጤት ግብፅ ትቀበላለች" ሲሉም አረጋግጠዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው "በህዳሴው ግድብ ዙርያ ግልፅ ለመሆን እየጣርን ነው። አሁን የቀረበውን ምክረ-ሃሳብንም እናየዋለን። የሦስት ሃገራት ጉዳይ ስለሆነ በጥንቃቄ መያዝና መታየት አለበት" ብለዋል።

ሃገራቱ በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በተጠናከረ መንገድ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ሚንስትሮቹ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።