በሀሰተኛ መድሃኒት ሰዎች እየሞቱ ነው

የሚያለቅስ ልጅ Image copyright Science Photo Library

ልጅዎ በጠና ታሞቦታል እንበል። የሚታይበት ምልክት ሁሉ በቀዳሚነት ዓለም ላይ የልጆች ገዳይ የሆነው ወባ ነው። ቢሆንም መድሃኒት እሰጠዋለው ብለው ይፅናናሉ። መድሃኒቱንም ለልጅዎ ይሰጡታል።

መድሃኒቱ ልጅዎን እያሻለው አለመሆኑ ግን ያሳስብዎታል። ምክንያቱ ደግሞ የገዙት መድሃኒት ሀሰተኛ በመሆኑ ነው።

ይህ ብዙዎች ሳያውቁ የተጎዱበት አሰቃቂ እውነታ ነው። ከዚህ ጀርባ ያሉት ደግሞ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው አፍሪካ ውስጥ በዓመት 120ሺህ ሰዎች በሀሰተኛ የወባ መድሃኒት ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ። መድሃኒቶቹ ከደረጃ በታች ናቸው አልያም መያዝ ያለባቸውን ንጥረ ነገር ፈፅሞ አልያዙም።

ሀሰተኛ መድሃኒቶች ብቻም ሳይሆኑ የጥራት ደረጃቸው የወረደ መድሃኒቶች እንኳን የመድሃኒት መላመድን ስለሚያስከትሉ ነገሩ በጣም አደገኛ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ካሉት መድሃኒቶች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሀሰተኛ ናቸው። እነዚህ ሃሰተኛ መድሃኒቶች ደግሞ በየመድሃኒት ቤቱ፣ በየክሊኒኩ፣ በየመንገዱና በድረ-ገፆች ጭምር ይሸጣሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ውስን አቅም ያላቸው ተቋማት ይህን ለመከላከል እየተንቀሳቀሱ ነው።

Image copyright Getty Images

ቀላልና ርካሽ

ለምሳሌ ስፕሮክሲል የተባለ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ለችግሩ ቀላል መፍትሄ ፈጥሯል። ይህ ኩባንያ መድሃኒት አምራች ድርጅቶች እንዲመዘገቡና የሚያመርቷቸው መድሃኒቶች ማሸጊያ ላይ ኩባንያው የሚሰጣቸውን ስቲከር እንዲለጥፉ ያደርጋል።

መድሃኒቶቹን የሚገዙ ሰዎች ስቲከሮቹን በመፋቅ የሚያገኟቸውን ቁጥሮች ለስፕሮሲስ ኩባንያ በስልክ መልዕክት ይልካሉ። ኩባንያውም መድሃኒቱ ትክክለኛ ስለመሆኑ በመልዕክት ማረጋገጫ ይሰጣል።

ኩባንያው 24 ሰዓት የማረጋገጥ አገልግሎት ይሰጣል። እስካሁን 70 የሚሆኑ መድሃኒት አምራቾች የተመዘገቡ ሲሆን እስካለፈው የፈረንጆች ዓመት ድረስ 28 ሚሊዮን ማረጋገጫዎችንም ሰጥቷል።

"ይህ ርካሽ የሆነ የደህንነት እርምጃ ነው"ይላሉ የስፕሮክሲል ቃል አቀባይ የሆኑት ጋባሞላዩን። ይህ የኩባንያው ሥርዓት በአፍሪካ በኬንያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያና ማሊ ተግባራዊ ሆኗል።

ቢሆንም ግን ሥርዓቱ በአፍሪካ በደንብ ሊስፋፋ ይገባል። ምክንያቱም የሀሰተኛ መድሃኒቶች ገበያ አሁንም እንደደራ ነውና።

ከአስር ዓመታት በፊት ተመሳሳይ "በሞባይል ያረጋግጡ" የሚል ሥርዓት የፈጠረ ኩባንያም ነበር። ይህ ሥርዓትም በተመሳሳይ መልኩ መድሃኒት ላይ የተለጠፉ ቁጥሮችን በስልክ መልዕክት በመላክ ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው።

ኩባንያው እንደሚለው ሥርዓቱ በናይጄሪያ ከመድሃኒት ምርትና ሽያጭ ሰንሰለት ጋር በተያያዘ ማረጋገጫዎችን በመስጠት ለቅኝትና ቁጥጥር አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።

ይህ ደግሞ ተቆጣጣሪዎችንና አምራቾችንም ጠቅሟል።

ይህ ኩባንያ በ12 የአፍሪካና የእስያ አገራት የሚንቀሳቀስ ሲሆን በተለይም በአፍሪካ ሃሰተኛ መድሃኒቶች በመያዛቸው 75 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰወች መጠቀማቸውን ድርጅቱ ይገልፃል።

በስልክ መልእክት የመድሃኒቶችን እውነተኝነት ለማረጋገጥ ከመሞከር ባሻገር የመድሂኒት ተቆጣጣሪ አካላትን ብቃት የመገንባት እርምጃዎችም በዓለም አቀፍ መድሃኒት ተቆጣጣሪ ድረጅቶች ተሰጥቷል።

የመድሃኒት ቁጥጥር ህጎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ዛሬም ሰዎች በሀሰተኛ መድሃኒቶች ህይወታቸውን እያጡ ነው።

Image copyright Sproxil

ጥረቶቹ ለምን አልተሳኩም?

የተለያዩ የቁጥጥር ሥርዓቶችን የዘረጉ ኩባንያዎች እያሉና ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ሰዎች ለምን በሀሰተኛ መድሃኒቶች ይሞታሉ የሚለው አሁንም የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ከኩባንያዎቹ አንዱ እንደሚለው ብዙዎቹ ሃሰተኛ መድሃኒቶች የሚሰሩት እስያ ውስጥ ነው። የሃሰተኛ መድሃኒቶቹ ገበያ ስፋት ከቁጥጥር ሥራው ጋር ሲነፃፀር ገበያው በጣም ጠንካራ ነው።

ይህ ማለት ደግሞ ቁጥጥሩ ላይ በጣም ሊሰራ ይገባል። የትልልቅ ዓለም አቀፍ መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች የቁጥጥር ሥርዓቱን ለመቀላቀል መዘግየታቸውም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

በተጠቃሚዎችና በአምራቾች ዘንድም ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን የስፕሮክሲል ሥራ አመራሮች ይገልፃሉ።

አመራሮቹ እንደሚሉት ሙስና ደግሞ ችግሩን ያባባሰ ሌላው ጉዳይ ነው። በዚህ ምክንያት ሃሰተኛ መድሃኒቶች መረጃው እያለና እየታወቀ እርምጃ ሳይወሰድባቸው እንዲያልፉና ገበያ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል።

ስለዚህ ከቁጥጥር ጎን ለጎን ተጠያቂነት ሊኖርና ቅጣቶች ሊጠብቁ እንደሚገባ ይገልፃሉ።

ደካማ የመድሃኒት ቁጥጥር ህግና ደካማ ተቆጣጣሪ አካል ባለባቸው አገራት ዛሬም የሃሰተኛ መድሃኒቶች ገበያ እየደራና ለአንቀሳቃሾቹ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያስገኘ ነው።

ይህ የሚያሳየው ሃሰተኛ መድሃኒቶችን ለማስወገድ ቴክኖሎጂ ብቻውን ምንም የሚፈይደው ነገር አለመኖሩን ነው። ይልቁንም የህብረተሰብን ግንዛቤ መጨመር፣ የቁጥጥር ሥርዓትን ማጠናከርና ህጎችን ማጥበቅ የግድ ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች