በጽኑ የታመሙ ሕፃናትን በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ካለችው ደማስቆ ማስወጣት ተጀመረ

ታካሚ ሕፃናትን ከደማስቆ ማስወጣት ተጀመረ Image copyright ICRC

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር እንዳስታወቀው ህክምና በማግኘት ላይ የሚገኙ ህፃናት በታጣቂዎች ከተያዘው ሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ገጠራማ ክፍል ማስወጣት ተጀምሯል።

ማሕበሩ በይፋዊ ትዊተር ገፁ እንዳሳፈረው "በጽኑ" የታመሙ ህፃናትን ከምስራቅ ጉታ አካባቢ ወደ መሃል ከተማ ደማስቆ የማዛወር ሥራ እየተከናወነ ነው።

ባለፈው ሳምንት መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገ አንደ የእርዳታ ድርጅት ፕሬዝደንት በሻር አል-አሳድ ሰባት የካንሰር በሽታ ያለባቸውን ሶሪያውያን ህፃናት ከቦታው ለማስወጣት እቅድ ላይ እንደሆኑ አስታውቆ ነበር።

ከመንግሥት ቁጥጥር ወጥቶ አሁን ላይ በታጣቂዎች እጅ በሚገኘው የምስራቅ ጉታ አካባቢ ቢያንስ 130 ህፃናት በፀና ታመው እንደሚገኙ ይታወቃል።

የተባበሩት መንግሥታት መግለጫ እንዳሚያሳየው 400 ሺ ሰው ከሚኖርባት ምስራቅ ጉታ 12 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።

ባሳለፍነው ማክሰኞ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር ህፃናቱን ከአካባቢው ሊያስወጡ የመጡትን አምቡላንሶች ፎቶ ይፋ አድርጎ ነበር፤ ቢሆንም ምን ያህል ሰዎች ከቦታው እንደሚወጡ ግን ምንም የተሰጠ መረጃ የለም።

የሶሪያ መንግሥት ስለሁኔታው እስካሁን የሰጠው ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ የለም።

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበርና የተባበሩት መንግሥታት ምስራቅ ጉታ ለእርዳታ ምቹ እየሆነች እንዳይደለም በማለት ቦታው ለህክምና እርዳታ ክፍት እንዲሆን ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በቅርቡ የፕሬዝደንት በሻር አል-አሳድ መንግሥት ቦታው በተቆጣጠሩት ታጣቂዎች ላይ እርምጃ በመውሰዳቸው ሰላማዊ ሰዎች ሕይዋታቸውን ማጣታቸውንና በርካቶች ለምግብ እርዳታ ተጋለጭ እንደሆነ ተዘግቦ ነበር።

የበሻር አል-አሳድን መንግሥት እንደሚደግፉ የሚታመኑት ሩስያና ኢራን በዚህ በኩል ደግሞ ታጣቂዎችን ትደግፋለች የምትባለው ቱርክ ምስራቅ ጉታን "ግጭት የፀናበት ቀጣና" በማለት ሰይመውት እንደነበርም አይዘነጋም።