ለመከላከያ ምስክርነት የተጠሩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይገኙ ቀሩ

ፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት Image copyright FSC

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ለመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ተጠርተው የነበሩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፍርድ ቤት ሳይገኙ ቀሩ።

የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አብዱል ጀባር ሁሴን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ለተጠሩት ባለሥልጣናት በአካል መስጠታቸውንና በነገው ዕለት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ትናንት (ማክሰኞ) በአቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠርተው ያልመጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን በተመለከተም በፖሊስ ተገደው እንዲቀርቡ ተብሎ የቀረበውን ጥያቄን በተመለከተም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዛ አልሰጠም።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው የ14ኛ ተከሳሽ የደረጀ መርጋን የመከላላያ ምስክር አድምጧል።

የ4ኛ ተከሳሽ የአቶ በቀለ ገርባ የመከላከያ ምስክር እንዲሆኑ የተጠሩት አቶ አንዱዓለም አራጌ ታስረው የሚገኙበት ማረሚያ ቤት ለምስክርነት ሳያቀርባቸው ቀርቷል።

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም አራጌ ከባድ ፍርደኛ ስለሆኑ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል።

ነገር ግን ጠበቃ አብዱልጀባር ፍርድ ቤቱ ለማረሚያ ቤቱ ጥብቅ ትዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀው፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዱዓለም አራጌን ለነገ ችሎት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የጤንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ የተነገረው አቶ በቀለ ገርባ ህክምና እንዲያገኙ ያጋጠማቸውን የጤና ችግር አሳሳቢነት በመጥቀስ በአስቸኳይ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠበቃቸው ጥያቄ አቅርበው ፍርድ ቤቱ በጥያቄው ላይ ምላሽ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ የፍርድ ቤት ዜና የወልቃይት ኮሚቴ ተከሳሽ፤ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎታል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ ዳኛው በወልቃይት ጉዳይ ላይ ከእኛ አቋም ተቃራኒ የሆነ ፅሁፍ በድረ ገፅ ላይ በማስፈራቸው ሚዛናዊ ሆነው ፍትህ ሊሰጡን አይችሉም በሚል ነበር ከችሎት እንዲነሱ ጥያቄ ያረቡት።

ነገር ግ ፍርድ ቤቱ የተፃፈው ጉዳይ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከተከሰሱበት ወንጀል ጋር በቀጥታ አይያያዝም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።

ተያያዥ ርዕሶች