የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻዎች

ሶሻል ሚዲያ

የተለያዩ ጉዳዮች ወትዋችና አስታዋሽ ይፈልጋሉ። ለዚህም ነው የማህበራዊ ሚዲያ አራማጆች (አክቲቪስቶች) ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አንስተው ትኩረት እንዲያገኙ ጥረት የሚያደርጉት።

ለዚህ ደግሞ መነሻ የሆነን ሃሳብ ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ-ገፆች የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞችን እናስታውስ በሚል የተካሄደው ዘመቻ ነው።

የአራማጅነት የተለያዩ መልኮች

እአአ 2011 በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ተማሪዎች የተቋቋመው የ'የለው ሙቭመንት' መሥራች ከሆኑት መካከል ወ/ት ሕሊና ብርሃኑ አንዷ ነች። ወ/ት ህሊና የሥርዓተ-ፆታ እና ሕግ መምህርት ስትሆን የእንቅስቃሴውን ጅማሬ እንዲህ ታስታውሳለች።

"በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችው አበራሽ ላይ የደረሰው ጥቃት እና እሱን ተከትሎ በተለየዩ መገናኛ ብዙሃን የተነሳው ውይይት ለእንቅስቃሴው መመስረት ሰበብ ሆኖናል።"

እንዲህ አይነት ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሲደርስ ሁሉም 'የአንድ ሰሞን ጀግና' ይሆናል የምትለው ወ/ት ሕሊና፤ ከዚያ በኋላ ሁሉም ወደ የዕለት ተግባሩ ሲገባ የሴቶቹ ጥቃት ይረሳል ስትል ትተቻለች።

"ስለዚህ እኛ ቀጣይነት ያለው ውይይት እና ግንዛቤ ለመፍጠር በማሰብ መስራት ጀምረናል" ባይ ነች።

'ሴታዊት' በተሰኘው ሌላኛው እንቅስቃሴ ውስጥ የኮሙኑኬሽን አስተባባሪ የሆነችው ወ/ት ፍራኦል በላይ ደግሞ ሴታዊት በማህበረሰቡ ውስጥ አይነኬ የሚባሉ ነገሮች ላይ ውይይት ለመፍጠር እየሰራ ነው ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

"ውይይቱ ግን ቀጣይነት አንዲኖረው ክብረ በዓላትን ብቻ እየተከተልን ሳይሆን እኛ ራሳችን እያቀድን የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን እናደርጋለን።"

የዞን ዘጠኝ ጦማሪ የሆነው በፍቃዱ ኃይሉ በተከታታይ ያደረጓቸውን የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻዎችን ያስታውሳል።

"በዋናነት በአራት ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ዘመቻዎችን አድርገናል። እነዚህም ሕገ-መንግስቱ ይከበር፣ ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት ለሁሉም ይሁን፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት ይከበር፣ ኢትዮጵያዊ ሕልም አብረን እናልም የሚሉ ነበሩ።''

የፌስ ቡክ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቡድን አቋቁመው ከቀን መረጣ እስከ ምስል ዝግጅት እንዲሁም ዘመቻውን የሚያግዙ የተለያዩ ጽሁፎች እና መሪ ቃሎችን በደንብ አብላልተው እንደሚዘጋጁ ይናገራል።

ከዚህ በተለየ ደግሞ ሌሎች የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና አካባቢያዊ ለውጥን ለማምጣት ወይንም ንቃት ለመፍጠር የሚሰሩ አሉ። ከእነዚህ ዓይነት የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ አራማጆች መካከል በሰፊው የሚታወቁት 'ድምፃችን ይሰማ' እና አሁን ደግሞ 'የህሊና እስረኞችን እናስብ' በሚል እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ነው።

በዚህ ሳምንት የተጀመረው 'የህሊና እስረኞችን እናስብ' የፌስ ቡክ እንቅስቃሴን ሃሳብ ያመነጩት አቶ ጌታቸው ሽፈራው ዓላማው ''የተዘነጉ የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞችን ለአንድ ቀን ማስታወስ እና ፍትሕ እንዲሰጣቸው መወትወት ነው'' ይላሉ።

ትኩረት የተነፈጋቸው ጉዳዮች

በአገራችን በጣም አስፈላጊ ሆነው፤ ነገር ግን የተዘነጉ በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዳሉ እሙን ነው።

ለአቶ ጌታቸው ደግሞ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ የተዘነጋ ነው። ''እስረኞቹ የማንነት ወይንም የሀይማኖት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ በርካታ በደል ይደርስባቸዋል'' ይላሉ አቶ ጌታቸው።

''ይህ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በነበሩት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተባብሷል። እነዚህ ታሳሪዎች የተለያየ በደል የደረሰባቸው ሲሆን ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን እስኪያስረዱ ድረስ ማንም አይሰማቸውም'' ሲሉም ይናገራሉ።

በጠባብ ክፍሎች የደረሰባቸውን በደል ህዝብ በሰፊው እንዲሰማላቸው፤ በዳዮች ተለይተው ቢቻል ዛሬ ባይሆን ነገ ለፍርድ እንዲቀርቡ መረጃው እንዲሰራጭ ማድረግ አልተቻለም ሲሉ አቶ ጌታቸው ይጨምራሉ።

ስለዚህ በዚህ ሳምንት የተካሄደው ዘመቻ ስለ እስረኞች የሚያውቅ ሁሉ ያለውን መረጃ እንዲያካፍል፣ በደል ስለ ተፈፀመባቸውንና በደል ስለፈፀሙ ሰዎች መረጃ እንዲለዋወጥ፣ በደል የፈፀሙ እንዲጠየቁ፣ በደል የደረሰባቸውም የተቻለው ሁሉ እንዲደረግላቸው ለመመካከር አንደሆነ ገልፀዋል።

ማህበራዊ ሚዲያን ለለውጥ

በሥርዓተ-ፆታ ላይም ሆነ እንዲህ የእስረኞች መብት እንዲከበር የሚወተውቱ ወገኖች በጋራ የሚስማሙበት ነገር ቢኖር ማህበራዊ ሚዲያ ምንም እንኳን ጓዘ ብዙ ቢሆንም ሃሳባቸውን ወደ ብዙሃኑ ለማድረስ እንደ ድልድይ ሆኖ አገልግሏቸዋል።

''በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የያዝነው ሃሳብ መወያያ እንዲሆን እና ግንዛቤ እንዲፈጠር አጥብቀን እንሰራለን'' የምትለው ሕሊና የሚያነሷቸው ሃሳቦች ተገቢውን ተፅእኖ እንዲፈጥሩ በጥናት የተደገፈ ዘመቻዎችን እንደሚያካሂዱ ይናገራሉ።

ፍራኦልም በበኩሏ ''ዋነኛ አላማችን በፌስ ቡክ ማህበረሰብ መካከል ውይይትን መፍጠር ነው። እድለኛ ከሆንን ትልልቅ የመገናኛ ብዙሃን ሃሳቡን ወስደው ለሰፊው ህዝብ ያደርሱታልም'' ብላለች።

በማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ የሚያነሱት ጉዳዮችን የተለያዩ ግለሰቦች ወደየራሳቸው እየወሰዱ ለሌሎች ያጋራሉ፣ ታሪካቸውን ያካፍላሉ እንዲሁም የፌስቡክ፣ ቲውተር እና ኢንስታግራም ገፅ ፎቶዎቻቸውን በዘመቻው መለያ ወይንም መሪ ቃል ይቀይራሉ። ይህ ደግሞ ውይይት የመፍጠር አላማቸውን እንደሚያሳካ ታምናለች።

በርግጥ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚነሱ ዘመቻዎችን የሚደግፍ እና የሚከተል ብቻ ሳይሆን የሚነቅፍም አለ የሚሉት ሕሊና እና ፍራኦል ከደጋፊዎቻችን ብቻ ሳይሆን ከነቃፊዎቻችንም እንማራለን ብለዋል።

በፍቃዱ በበኩሉ ''ያካሄድናቸው ዘመቻዎች ውጤታማ ነበሩ ማለት እችላለሁ" ይላል። በእኛ ዘመቻዎች በርካቶች ተነቃቅተዋል። ተነቃቅተውም ያጋራናቸውን ነገሮች ተቀባብለዋቸዋል።''

በተለይ በሕገ-መንግሥት አንቀፆች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደቻሉና ከምንም በላይ ለመንግሥት አካል ጋር ሃሳባቸው ደርሷል ብሎ ያምናሉ።

አቶ ጌታቸውም ከዚህ የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ የበርካቶችን ተሳትፎ እና ውይይት እንደሚጠብቁ ይናገራሉ።

ተግዳሮቶቹ ምን ምን ናቸው

"የበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ተደራሽነት እና ፍጥነቱ አስቸጋሪ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ጥሩ የተሳታፊዎች ምላሽ" የሚሉት አቶ ጌታቸው ችግሩን ለማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻ እንደ ዋነኛ ተግዳሮት ያስቀምጡታል።

አቶ በፍቃዱ በበኩላቸው በቂ ዝግጅት አለማድረግ፣ የማይጋብዙ መሪ ቃሎችን ማቅረብ፣ ሞገደኛ የሆኑ ቃላትን መጠቀም፣ ዘመቻው የሚካሄድባቸው ቀናት በሌላ አጀንዳ አለመያዛቸውን አለማረጋገጥ ተግዳሮቶች ናቸው ይላሉ።

የሚነሱ የዘመቻ ሃሳቦችን በበጎ የማይመለከቱ አካላትም ከተግዳሮቶቹ መካከል ይጠቅሳሉ።

ቢሆንም ግን የማህበራዊ ድረ-ገፅ አራማጅነት ሁሉም ሃሳቦች ተነስተው ውይይት በማካሄድ ግንዛቤ ተፈጥሮ ችላ የተባሉ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ እንዳስቻለ ያምናሉ።