ዘርፈ ብዙዋ ወጣት ጥበበኛ

'ቃተኛ' የግጥምና ስዕሎች ስብስብ መድብል Image copyright Rahel Buluts
አጭር የምስል መግለጫ 'ቃተኛ' የግጥምና የስዕሎች መድብል

ወጣት ናት። ከቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት "ወጣት የልማት ጀግና" በሚል የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብላለች። በኪነ ጥበብ ዘርፍ፣ የዕደ ጥበብ እና የሥዕል ሥራዎች ላይ በመትጋት በዘርፉ የራሷን አስተዋጽዖ እያበረከተች ትገኛለች።

በታህሳስ 2007 ዓ.ም በሰሜናዊቷ ኮኮብ መቐለ ከተማ "ራሄል አርት ጋለሪ" በማለት የከፈተችው በትግራይ ብቸኛ የሆነው ጋለሪ፤ ወጣቶች ጥሩ ጊዜ የሚያሳልፉበት፣ የሚወያዩበት መድረክ በመሆን ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል።

ከዚህ በተጨማሪ መድረኩ፤ አጫጭር ግጥሞች እና የተለያዩ የሥነ-ፅሑፍ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ወጣቶችን መጽሐፍ እስከማሳተም ደርሷል።

በራሄል አርት ጋለሪ ውስጥ ያሉት ሥዕሎች እና የዕደ-ጥበብ ሥራዎችም ጥልቅ ምናባዊ መልዕክት የሚሸጋገርባቸው ናቸው። የድርጅቱን ባለቤት ጨምሮ ሌሎች በአርት ጋለሪው ሥዕሎቻቸውን የሚያስተዋውቁና ለገበያ የሚያቀርቡ ወጣቶች ሥራዎቻቸውን በጋለሪው ለእይታ ያቀርባሉ።

አርት ጋለሪው ሥራ ሲጀምር፤ ከአሁን በፊት ያልተለመደ ስለነበር አትራፊ ያለመሆን፣ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳለፉበት የመዝናኛ ቦታ አድርጎ ለመውሰድ እና ሌሎች ችግሮች የነበሩ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ አመለካከት እየተለወጠ መሆኑን ራሄል ትናገራለች።

በሰፊው የአትክልት ስፍራ ውስጥ በኪነ-ጥበብ ሥራዎች ያሸበረቀው የጥበብ ማዕከል ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች በነፃ መጻሕፍት ያነባሉ። ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎትን ያገኛሉ። ከዚህ ባለፈ ደግሞ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች እና ባህላዊ ይዘት ያሏቸው ዕቃዎች በማዕከሉ ይሸጣሉ። ሳምንታዊ የሥነ-ጽሑፍ መድረክም ይዘጋጃል።

ከዚህ ባሻገር ጋለሪው የጥበብ ትምህርት ቤት በመሆንም በማገልገል ይገኛል። ሕፃናት እና ወጣቶች አጫጭር የክረምት ሥልጠናዎች ያገኛሉ።

"ይህ አርት ጋለሪ ለእኔ ኢንቨስትመንት ነው። በአስተሳሰብ ደረጃ ሰዎች የሚታነጹበት እና ብዙዎች የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታቸውን የሚያሳድጉበት እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ ጥበብ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው" ትላለች ራሄል ብሉፅ።

በርካታ ፈተናዎችን ያለፈችው ራሄል አሁን አርት ጋለሪው "ለጥበብ የነበረ የተሳሳተ አመለካከት ቀይሯል" ትላለች።

ጋለሪዉ ምን ጠቀመ?

በራሄል አርት ጋለሪ ዘወትር ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሚዘጋጀው የሥነ-ጽሑፍ መድረክ ላይ ሲቀርቡ የነበሩ አጫጭር ጽሑፎችና ግጥሞች የሚያነሷቸው ሃሳቦች የብዙዎች መነጋገርያ እየሆኑ እንደመጡ ከመድረኩ የማይጠፉ ታዳሚዎች ይናገራሉ።

ሦስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ያከበረው 'ራሄል አርት ጋለሪ' ባለፉት ዓመታት መድረኩ ላይ ሲቀርቡ ከነበሩት ግጥሞች፤ በገላጭ ሥዕሎች ታጅበዉ በአንድ መጽሐፍ ታትመዋል። በዚህ መጽሐፍም ላይ 40 ገጣሚያን እና 20 ሠዓሊያን ተሳትፈዋል።

ከሠዓሊዎቹ መካከል አንዷ የሆነችው ምንያ ይህ መድረክ ሴቶችና ወጣቶች የሚሳተፉበት፣ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እንደሆነ ትናገራለች።

"በቀጣይ የሥዕል ጥበብ በሴቶች እንዲያድግ እፈልጋለሁ። ሁላችንም በመተጋገዝ ጥበቡ እንዲያድግና ተጨማሪ አርት ጋለሪ እንዲኖረን ደግሞ እመኛለሁ" ትላለች ምንያ።

በዕለተ ቅዳሜ በሚዘጋጀው የሥነ-ጽሑፍ መድረክ ላይ ባህላዊ ትዉፊቶችን በማቅረብ የሚታወቀዉ አስገዶም ተወልደ ደግሞ ጋለሪው ከተከፈተ ጀምሮ ብዙ ጸሐፊያን ሥራዎቻቸውን ማምጣት መጀመራቸውን ይገልጻል።

"ማሕበራዊ ችግሮችን የሚዳስሱ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች በድፍረት ይቀርቡ ነበር። ባህላዊ ትውፊቶች፣ ሥነ-ቃሎች እና ሌሎችንም በማቅረብ ሰዎች እንዲቀራረቡ አድርጓል" ይላል።

Image copyright Rahel Art Gallery
አጭር የምስል መግለጫ ራሄል ብሉጽ

ዘርፈ ብዙዋ ራሄል

የልብስ ስፌትና ዲዛይን፣ ኢንጅነሪንግ፣ አርክቴክቸር እና አርባን ፕላኒንግ ራሄል በዲግሪ ፕሮግራም የተማረቻቸው መስኮች ናቸው።

የስምንት ዓመት ልጅ ሆና ዲዛይን የጀመረችው ራሄል፤ እየሠራችው ላለችው ሥራ በያንግ አፍሪካ ሊደር ሺፕ ኢኒሽየቲቭ (ያሊ) በኬንያ ለሦስት ወራት ሥልጠና ወስዳለች። የአሜሪካ ኤምባሲም እውቅና የሰጣት ሲሆን የኦባማ ማንዴላ ፕሮጀክትም አባል ነች።

ሴቶች እራሳቸው እንዲችሉ የሚደግፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግም በማሽን የማይሠሩ የሸክላ ሥራዎችን በማምረት እንዲያቀርቡላት በማድረግ የገበያ ትስስር እየፈጠረችላቸው ትገኛለች።

በቀጣይም የጀመረችውን ሥራ በማሳደግ የዕደ-ጥበብ ሥራዎች እንዲሰፋፉ የሙዚቃ መድረኮች የሚዘጋጅበት፣ ሰፊ አረንጓዴ ቦታ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የቲያትር አዳራሽና ሌሎችንም ያሟላ ማዕከል እንዲኖር በመሥራት ትገኛለች።