ቻይና የዝሆን ጥርስ ንግድን አገደች

ዝሆን Image copyright Getty Images

ቻይና የዓለም ትልቁ የዝሆን ጥርስ ገበያ ሆና ቆይታ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በሃገሯ የሚከናወን ማንኛውም የዝሆን ጥርስ ግብይት ሕገ-ወጥ እንደሆነ አውጃለች።

ይህ ውሳኔዋም የቀሩትን ዝሆኖች ለመጠበቅ ለሚደረገው ጥረት አንድ ትልቅ እርምጃ ነው ተብሎ ተወድሷል።

ዝሆኖችን ለመታደግ የሚሰሩ ተቆርቋሪዎች እንደሚያምኑት 30ሺህ ያህል የአፍሪካ ዝሆኖች በየዓመቱ በአዳኞች ይገደላሉ።

የቻይና መንግሥታዊ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ባለፈው ዓመት የዝሆን ጥርስ ዋጋ በ65 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

በተጨማሪም ወደቻይና ሲገባ የሚያዘው የዝሆን ጥርስ መጠን በ80 በመቶ መቀነሱም ዥንዋ ዘግቧል።

የዝሆን ጥርስ ንግድን የማገዱ ውሳኔ ይፋ የሆነው በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ሲሆን ተግባራዊ የሆነውም በዓመቱ የመጨረሻ ዕለት ጀምሮ ነው።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በዝሆን ጥርስ ምርትና ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 67 ተቋማት የተዘጉ ሲሆን የተቀሩት 105ቱ ደግሞ እሁድ ዕለት እንደተዘጉ ተነግሯል።

የዱር እንሰሳ ደህንነት ተከራካሪ የሆነው ተቋም ዜናውን ተከትሎ ''የዓለም ትልቁ የዝሆን ጥርስ ገበያ በሮች ሲዘጉ ማየት እጅጉን ያስደስታል'' ብሏል።

የዝሆን ጥርስ ዋነኛ የመገበያያ ስፍራ እንደሆነች የሚነገርላት ሆንግ ኮንግን ግን አዲሱ ሕግ የማይመለከታት መሆኑ አሳሳቢ ነው ተብሏል። ነገር ግን ግዛቲቱ የእራሷን የዝሆን ጥርስ ንግድን የሚያግድ ሕግ ለማውጣት በሂደት ላይ መሆኗም ተነግሯል።