በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦች እንደሚፈቱ እየተነገረ ነው

የአራቱ ድርጅቶች መሪዎች Image copyright PM Office facebook

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦች ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት እንዲፈቱ መወሰኑን ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የፌስ ቡክና የትዊተር ገፁ ላይ እንዳሰፈረው "በአቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙና የተፈረደባቸው የተለያዩ ፖለቲከኞችም ሆነ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት እንዲፈቱ ተወስኗል'' ሲል አስፍሯል።

ከሰዓታት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ከላይ የሰፈረው ፅሁፍ ተሻሽሎ "በራሳቸው የጥፋት ድርጊት ምክንያት በአቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙና የተፈረደባቸው የተለያዩ ፖለቲከኞችም ሆነ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ እንዲፈቱ ተወስኗል" በሚል ቀርቧል።

የኢህአዴግ አባል ድርጅት መሪዎች ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀውን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብስባ ውሳኔን በተመለከተ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ ነው ይህ ዜና የወጣው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ከወጣው መረጃ በተጨማሪ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ዜና አስፍሯል።

በተጨማሪም የተለያዩ ሰቆቃዎች በእስረኞች ላይ እንደሚፈፀምበት ሲነገር የቆው "ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማዕከል እንዲዘጋ ተደርጎ ሙዝየም እንዲሆን ተወስኗል'' ተብሏል።

"በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረውና በተለምዶ ማእከላዊ በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማእከል እንዲዘጋ ተደርጎ ይህ እንዳይደገም ለማድረግ ማእከላዊ ሙዝየም እንዲሆን ተወስኗል:: በአለማቀፍ ስታንዳርድና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባፀደቀው የሰብአዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር መሰረት አዲስ የምርመራ ተቋም ተቋቁሞ በሌላ ህንፃ ስራ ጀምሯል" ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማለታቸውን የፅ/ቤታቸው የፌስ ቡክ ገፅ አስነብቧል።

ተያያዥ ርዕሶች