የጣና ሐይቅን ሌሎችም አረሞች ያሰጉታል

አርሶ አደሮች እምቦጭ እየነቀሉ
የምስሉ መግለጫ,

ጣና ሐይቅ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው

ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው ወንዴ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ናቸው። በጣና ዙሪያ መወለዳቸውን የሚገልጹት ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው ላለፉት 15 ዓመታትም በጣና ሐይቅ ላይ በግላቸውም ሆነ ከተማሪዎቻቸው ጋር የተለያዩ ምርምሮችን አድርገዋል።

ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሐይቁ ዙሪያ ከመሥራታቸውም በላይ በጣና ውሃ ብክለት፣ የአካባቢው የውሃ አዘል መሬቶች፣ የጣና የውሃ ውስጥ ብዝሃ-ህይወት በአጠቃላይ በጣና ደህንነት ዙሪያ የተለያዩ ምርምሮችን አካሂደዋል።

"ሐይቁ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው። የአፈር መከላት፣ የደለል ክምችት፣ ተገቢ ያልሆነ የሥነ-ሕይወት አጠቃቀም፤ ልቅ ግጦሽ እና የባህር ሸሽ እርሻ ተጠቃሾች ናቸው። በተለይ ደግሞ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በሰሜናዊ ምሥራቅ የሐይቁ ክፍል የተከሰተው የእምቦጭ አረም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል" ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው።

እምቦጭ አረም ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። በ1965 ዓ.ም በቆቃ ሐይቅ ላይ ተከስቶ እንደነበር ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ።

የአረሙ ዋነኛ መነሻው ደቡብ አሜሪካ ብራዚል ነው። በጣና ሐይቅ ላይ ከመታየቱ በፊት በ2004 ዓ.ም መገጭ በሚባል ወንዝ ላይ ቀድሞ መከሰቱን ተመራማሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እጅግ አደገኛ የሆነው ይህ መጤ አረም ግንዱን እና ፍሬውን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች የሚራባ መሆኑ በፍጥነት እንዲስፋፋ አስችሎታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከመገጭ ወንዝ ላይ በመነሳት እስከ 100 ኪሎ ሜትር በመጓዝ የጣና ሐይቅ በአረሙ እንዲሸፈን አድርጓል ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥ እና በእምቦጭ አረም ላይ ያለው ዕውቀት አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። ከዚህ የከፋው ግን በአካባቢው አርሶ አደሮች እና ብዝሃ-ህይወት ላይ የሚያደርሰው ችግር ነው።

በሐይቁ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ደስታ ብርሃን እንዳሉት አረሙ ሐይቁን እያጠፋው ነው።

"ከብቶቹ ውሃ የሚጠጡበትን፣ ለልብስ ማጠቢያ እና ለተለያዩ ሥራዎች የምንጠቀምበትን ሃይቅ ልናጣው ነው" ይላሉ በቁጭት። "ከብቶችም አረሙን ሲበሉ ጤናኛ አይሆኑም ሥጋቸውም ሆነ ወተታቸው አይጣፍጥም" ሲሉ ይገልጻሉ።

በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ምትኬ ፈንቴ በበኩላቸው "አረሙ ከብቶቻችን እየገደለ ነው" ብለዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ከእምቦጭ በተጨማሪ አዞላ እና ኢፖማ የተሰኙ አረሞችም እየተከሰቱ ነው

"ጣና የገዳሙ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱም ሃብት ነው"

በጀልባ ሥራ የሚተዳደረው አባይነህ ምናለ አረሙ ለጀልባ ጉዞ የማይመች በመሆኑ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ይላል። የአሳ ምርትም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። "ድሮ ከአንድ ታንኳ 80 አሳ ይያዝ ነበር። አሁን ግን ከ15 አሳ በላይ አይገኝም" ሲል በሥራው ላይ ያለውን ችግር ይገልጻል።

ጣና ሐይቅን የቱሪዝም መስህብ ካደረጉት ነገሮች መካከል ከ20 በላይ ገዳማትን መያዙ ነው። ከገዳማቱ አንዱ በሆነው እንጦስ እየሱስ ገዳም በተገኘንበት ወቅት እማሆይ ወለተማርያምን "ጣና የገዳሙ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱም ሃብት ነው" ይላሉ።

እማሆይ ወለተማርያም፤ አረሙ አንጦስ እየሱስ ገዳም አካባቢ አለ መባሉ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። "አረሙ ሐይቁን ሊያደርቅብን ይችላል የሚል ስጋት አድሮብናል" ይላሉ።

"ምን ዓይነት ፈተና መጣብን ብዬ ነው ያዘንኩት" የሚሉት የገዳሙ አገልጋይ አባ ወልደሰንበት፤ የእርሻ ቦታዎችን የሚይዝ ከሆነ ህዝቡ ሊቸገር ይችላል። ይህ ደግሞ የእኛም ችግር ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው እንደሚሉት የተፈጥሮ ስጦታ ሆነው እምቦጭ በሌላው የተፈጥሮ ሃብት ጣና ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት እምቦጭ በትክክለኛ ቦታው ላይ ባለመገኘቱ ነው። "እጽዋት እንደ እጽዋት የሚቆጠረው በተፈጠረበት ሃገር ሲሆን በዛም እንደ ተፈጥሮ ፀጋም ይቆጠራል። ለምሳሌ ደንገል ለእኛ ተፈጥሮ ስጦታ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

"መጤ ሁሉ መጥፎ አይደለም" የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው እንደምሳሌ የሚያነሱት በቆሎ እና በርበሬን ነው። እነዚህ መጤ እጽዋት በሌሎች የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ጥቅም በመስጠት ላይ ናቸው። እምቦጭ ግን ከዚህ በተቃራኒ በውሃ፣ ሥነ-ህይወትና በሌሎች እጽዋት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ይላሉ።

"ጣና አስጊ ደረጃ ላይ ነው"

ችግሩን ለመቅረፍ ሦስት ዘዴዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው። የሠው ወይም የማሽን ጉልበትን በመጠቀም፣ እንደማንኛው አረም ኬሚካልን በመጠቀም ወይንም ደግሞ እምቦጭን ሊያጠፉ የሚችሉ ሌሎች እጽዋትን በማስፋፋት መሆኑን ይጠቁማሉ። ሃገራት እነዚህን ዘዴዎች ለየብቻ ወይንም በጋራ እንደ ችግሩ መጠን ይጠቀሙባቸዋል።

እነወይዘሮ ደስታም አረሙን ለማጥፋት እየጣሩ ነው። "የራሳችንን ሥራ በመተው ረቡዕ እና አርብ አረሙን ለመንቀል ወደ ሐይቁ መጥተን እንሰራለን" ይላሉ። "አባቶች እና እናቶች ለዓለም ይፀልያሉ። እምቦጭ አረም እንዲጠፋም እየጸለይን ነው" ሲሉ እማሆይ ወለተማርያም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጎንደር ዙሪያ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝማች ብርሃኑ እንደሚሉት አረሙን ለማጥፋት በጣና ዙሪያ የሚገኙ አምስት ቀበሌዎች እየተረባረቡ ነው። ችግሩ ስፋት ያለው በመሆኑ የአስር ቀበሌ ነዋሪዎችን ለማሳተፍ እየተሰራ ነው ይላሉ። "ይህ ግን በቂ አይደለም የማሽን ድጋፍ ከሌለ ጣና አስጊ ደረጃ ላይ ነው" ይላሉ።

"በቅንጅት አልተካሄደም"

አረሙን ለማጥፋት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ተማሎ በበኩላቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ውጤታማ መሆን መቻሉን ይገልጻሉ። እንደ ምጥራ አባ ዋርካ ያሉ ቀበሌዎች ነጻ መሆናቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በሰው ጉልበት የሚደረገው ሥራ በማሽን ካልታገዘ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አይሆንም። ይህን ለማድረግም ዩኒቨርሲቲዎች እና የተለያዩ ግለሰቦች እየሰሩ ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው ውሃው ለተለያዩ አገልግሎቶች ስለሚውል ኬሚካል ደግሞ ተመራጭ አይደለም ይላሉ። እምቦጭን የሚያጠፉ ሌሎች እጽዋትን ማስፋፋት ደግሞ እነሱም የሚያስከትሉት ችግር ሊኖር ስለሚችል ጥናት እየተደረገባቸው ይገኛል ብለዋል።

አረሙን ለማስወገድ በተደረገ ጥረት ውስጥ ህይወቱ የጠፋ ሰው መኖሩን እና በእባብ ተነድፈው ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉም የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር አያሌው፤ ሆኖም ሥራው "በቅንጅት አልተካሄደም" የሚል እምነት አላቸው።

ከሁሉም የሚያሰጋቸው ግን አሁን ያለው ችግር ሳይቀረፍ ከእምቦጭ በተጨማሪ አዞላ እና ኢፖማ የተሰኙ አረሞችም እየተከሰቱ መሆናቸው ነው።