በኢኳቶሪያል ጊኒ መፈንቅለ-መንግሥት ሊካሄድ ነበር

ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጉዬማ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጉዬማ

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ቅጥረኞች መፈንቅለ-መንግሥት ለማካሄድ ሙከራ እንዳደረጉ የሃገሪቱ መንግሥት ተናገረ።

ቢያንስ 30 የሚደርሱ ከቻድ፣ ከካሜሩንና ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የመጡ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ መያዛቸውን አንድ ሚኒስትር ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ታጣቂዎቹ የተያዙት ሃገሪቱን ከካሜሩን ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ከሮኬት ማስወንጨፊያ፣ ከጠመንጃዎችና ከጥይቶች ጋር ነው።

የፕሬዝዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ንጉዬማ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና በተደጋጋሚ ይከሰሳል።

የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እለት የሃገሪቱ ወታደሮች ከካሜሩን ድንበር አቅራቢያ ባለጫካ ውስጥ የነበሩትን ቅጥረኞች ለመበተን ተኩስ መክፈታቸውንና ከቅጥረኞቹ መካከልም አንዱን መገደሉን ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ አጎታቸው የነበሩትን ፍራንሲስኮ ማሲያስ ንጉየማን በመፈንቅለ-መንግሥት አስወግደው ስልጣን ከያዙ 40 ዓመት ሊሆናቸው ነው።

በሃገሪቱ ሬዲዮ የተነበበው መግለጫ የደህንነት ሚኒስትሩ ኒኮላስ ኦባማ ንቻማ መፈንቅለ-መንግሥቱ ስማቸውን ባልጠቀሱት ኃይሎች፤ በሚደገፉ ተቃዋሚ ቡድኖች በተቀጠሩ ታጣቂዎች ሊካሄድ እንደነበር መናገራቸውን ጠቅሷል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የከሸፈው በካሜሩን የደህንነት ተቋማት ድጋፍ ነው።

ኢኳቶሪያል ጊኒ ተመሳሳይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከዚህ በፊት ገጥሟት ነበር።

ኢኳቶሪያል ጊኒ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች ሃገራት መካከል አንዷ ብትሆንም አብዛኛው ሕዝቧ በድህነት ውስጥ ይገኛል።