የእስረኞች መፈታትና የማዕከላዊ መዘጋት ውሳኔ አንድምታዎች

የኢህአዴግ አባል ፓርቲ መሪዎች Image copyright PM Office facebook

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት ተቃውሞዎችን ተከትሎ ለውጦች ሊደረጉ ይችላል ተብሎ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ ቆይቷል። በተለይ ለሳምንታት የቆየው የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ አዲስ ነገርን ይዞ ይመጣል ተብሎ ነበር።

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መግለጫ ግን ጥቅል የሆኑ የመሻሻል እርምጃዎች ይወሰዳሉ ከማለት ያለፈ ነገር ስላልነበረው ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ነበር።

በተከታይ ቀናት የጋራ መግለጫ ይሰጣሉ የተባሉት የኢህአዴግ አባል ፓርቲ መሪዎችም ከዛሬ ነገ እየተባለ፤ ረቡዕ ለተወሰኑ የመንግሥት መገናኛ ተቋማት በሰጡት መግለጫ ግን አዲስ ነገር ተሰምቷል።

በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ከሌላው ጊዜ በተለየ ተከታታይ ፎቶግራፎችንና አነጋጋሪ የሆነውን ውሳኔ ለሕዝብ ሲያቀርቡ ነበር።

በቀዳሚነት የተላለፈው ባለ ሃያ ቃላቱ መልዕክት "በአቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የመሚገኙ የተለያዩ ፖለቲከኞች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ ተወስኗል::" የሚል ነበር።

ከዚያ በኋላ ግን ቃላት እየተቀየሩና እየተጨመሩ ለሰባት ጊዜ ያህል ለውጥና መሻሻል ተደርጎበታል። ይህም በተለይ ፖለቲከኞችን በተመለከተ የሰፈሩት አገላለፆች ጥርጣሬን አጭሯል።

ለሰባተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የቀረበው መልዕክትም 46 ቃላትን ይዞ "በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቢ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል::" የሚል ነበር።

እስካሁን ውሳኔው መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለፀ ነገር ባይኖርም በርካቶች ግን ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ እየገለፁ ነው።

መልካም ጅምር

በኪል ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ለሆኑት ዶ/ር አወል ቃሲም አሎ የመግለጫው መንፈስ ጥሩና የሚያበረታታ ነው።

ነገር ግን ለሁሉም የሕዝብ ጥያቄዎች መልስ እንደሆነ ሳይሆን መንግሥት ሊወስዳቸው ካሰባቸው እርምጃዎች መካከል እንደ አንድ ተደርጎ የሚወሰድ ከሆነ ጥሩ ዜና ነው ይላሉ።

የመብቶች ተከራካሪ እና ጋዜጠኛ ለሆነው አቶ ጌታቸው ሽፈራው ደግሞ ኢህአዴግ የ17 ቀኑን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ መሰረታዊ የሆነ እርምጃ እንወስዳለን ማለቱ ምን ሊወሰድ ይችል ይሆን የሚል ጥያቄ ፈጥሮበት ነበር ።

"ምክንያቱም አብዛኛው ሰብአዊ መብቶች የሚመለከቱት እስረኞችን ነው። ያ ደግሞ መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄ ስለሆነ አሁን ባሉት መልኩ አልጠበኩም።"

አቶ ገብሩ አስራት እንደሚሉት መጀመሪያም የፖለቲካ እስረኛ የሚባል ነገር መኖር አልነበረበትም። ማንም በፖለቲካ አመለካከቱ ሊታሰር እንደማይገባ በማመልከትም ሕገ-መንግሥቱን ይጠቅሳሉ። "ስለዚህ እርምጃው ቀድሞም ፖለቲከኞች ላይ የተከፈተ ጥቃት ነው። ማዕከላዊም የዚህ ጥቃት አካልና መሳሪያም" ነው ብለዋል።

ውሳኔውን እንደ አንድ አዎንታዊ እርምጃ ቢመለከቱትም የዘገየና ከብዙ ጥፋት በኋላ የተወሰደ መሆኑን ግን ይናገራሉ።

ይህ ውሳኔ መልካም ጅምር ነው፤ የሚሉት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በቂ የሚባል ግን እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"ለዚህች ሃገር ሰላም የሚሆነው ኢህአዴግ አሁን ያለበትን ሁኔታ መልሶ አይቶ ከሕዝቡ ጋር ተወያይቶ የሽግግር መንግሥት መመስረት ሲችል ብቻ ነው'' ይላሉ።

"ላለፉት 26 ዓመታት ብዙ ሕይወት ጠፍቷል፣ ደም ፈሷል፣ የሰዎች ኑሮ ተመሰቃቅሏል፣ በርካታ ሰዎች ሃገር ጥለው ተሰደዋል። ስለዚህ ይህን ጥያቄ ብቻ በመመለስ እርቅ ይፈጠራል ብለን አናምንም'' የሚሉት አቶ ሙላቱ የአሁኑ የመንግሥት ውሳኔ ሰላም ለማስፈን መልካም ጅምር በመሆኑ መቀጠል እንዳለበት ይጠቅሳሉ።

መንግትን ለዚህ ያበቃው ምንድን ነው?

ለዶ/ር አወል ኢህአዴግ የወሰደውን እርምጃ እንዲወስድ ያስገደደው፤ ''የነበረው ሕዝባዊ ጥያቄ በአባል ፓርቲዎች ላይ ያሳደረው ጫና እና ያም የፈጠረላቸው እድል ነው። ያንን ተጠቅመው እስከዛሬ ማድረግ ያልቻሉትን ነገር አሁን እያደረጉ ነው።''

"ሕዝቡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሳያቋርጥ ያደረገው ትግል ፍሬ ነው"ይላሉ።

ለዶ/ር አወል የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ትልቁ ጉዳይ ነው፤ ''ያለምንም ጥፋት ሕገ-መንግሥቱ የሚሰጣቸውን መብት ተጠቅመው ሕገ-መንግስቱ ይከበር ያሉ ሰዎችን መፍታት ከፍትህና የሕዝብ ጥያቄን ከመመለስ አንፃርም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል'' ባይ ናቸው።

"የሕዝብን ድምፅ እናሰማለን ብለው የቆሙ ሰዎችን ሕግን እና የሕግ-ሥርዓቱን ተጠቅሞ አስሯቸዋል። መንግሥት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች አሰፍናለሁ ካለ መደራደርም ካለበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ካለበት፣ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲያድጉ እንዲበለፅጉ ማድረግ ካለበት የመጀመሪያ እርምጃ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ነው።"

አቶ ጌታቸው ደግሞ ውሳኔው ከህዝቡ ጫና ባሻገር ኢህአዴግ ካርዱን የመጨረሱ ውጤት ነው ይላሉ። "ከዚህ በፊት የሰንደቅ አላማ ቀን፣ ከዚያም የሚሌኒየም ክብረ በዓልን በመቀጠል ደግሞ አባይን በማንሳት የሕዝቡን ጥያቄ ለማዳፈን ሞክሯል። "

አሁን ያለው እና ሕዝብ በቀዳሚነት የሚያነሳው ጥያቄ ደግሞ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ስለሆነ ''እፈታለሁ'' በማለት የፖለቲካ እስትንፋሱን ለማራዘም ይጠቀምበታል ሲሉ ይገልፃሉ።

"ከበቀለ ገርባ፣ ከመረራ እስከ አንዳርጋቸው ፅጌ ድረስ ያሉት እዛው እስርቤት ውስጥ ነው። ስለዚህ ለእኔ ህዝቡ እነዚህ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን ጥያቄ ነው ተቀብሎ ሲያሰማ ነበረው። አሁን ድምፁን የሚያሰማለት አካል ስለሌለ እሱ ራሱ አደባባይ ወጣ፤ ይህም ትልቅ ጫና ፈጠረ" ሲሉ ያስረዳሉ።

ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች መፈታት የታሰረውን ለውጥ መፍታትና የሌሎች ጥያቄዎችም መፈታት ስለሆነ ከነሱ መፈታት በኋላ ጥያቄው ይቀጥላል ሲሉ አፅንኦት ይሰጣሉ።

ከላዊ

ለአቶ ጌታቸው ማዕከላዊ ከሕግ ውጭ ከ4 ወር በላይ ታስሮ በኋላም የእስር ቤቱን ኃላፊዎች ከሶ የወጣበት ቦታ ነው።

ማዕከላዊንም ሲገልፀው "ሰማይ የሚናፈቅበት እስር ቤት ነው። እስረኛ 24 ሰዓት የማይከፈትለት፣ ፀሃይ ለ5 ወይም ለ10 ደቂቃ ብቻ የሚፈቀድበት፣ መፀዳጃ ቤት ጠዋት 11 እና ማታ 11 ሰዓት ብቻ የሚኬድበት ነው። በዚህ ላይ ድብደባው እና ሌሎች ማሰቃየቶችም አሉ።" ይላል።

በማዕከላዊ ሰቆቃ የደረሰባቸው ከሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑነ ጋዴዎችና አርሶ አደሮች አሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው በመግለጫው መሰረት የፖለቲካ እስረኞች ብቻ የሚፈቱ ከሆነ የእነዚህ ሰዎች እጣ ፈንታ ያሳስባቸዋል።

"ጥፍራቸው የተነቀለና የተኮላሹ ሰዎች ፍርድ ቤት በደላቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ሰዎች ደረጃውን ወደ ጠበቀ እስር ቤት ይዛወራሉ ከማለት፤ የተሰቃዩና ያለጥፋታቸው የታሰሩ ግለሰቦች መፈታት አለባቸው።"

ኢህአዴግ ማዕከላዊን መዝጋት የነበረበት የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ነው የሚሉት አቶ ገብሩ የዘገየ ቢሆንም ውሳኔው አንድ እርምጃ ነው ይላሉ።

ለዓመታት ፖለቲከኞችን እያሰሩ በአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት የማይታሰብ ነገር መሆኑን ተቃዋሚዎች ሲወተውቱ መቆየታቸውንም የሚያስታውሱት አቶ ገብሩ፤ ኢህአዴግ ግን ላለፉት በርካታ አመታት ማዕከላዊን አስቀጥሎታል።

የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትና ማዕከላዊን መዝጋት በአገሪቱ ከሚነሱ አጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ መልስ ብቻ መሆኑም ሊተኮርበት እንደሚገባም አቶ ገብሩ ያሳስባሉ።

ለአቶ ጌታቸው በሃገሪቱ ማዕከላዊ ብቻ አይደለም ማሰቃያ እና መመርመሪያ ሆኖ እያገለገለ ያለው።

"በማረሚያ ቤት ቃጠሎ ተጠርጥረው የተከሰሱት ሰዎች የተመረመሩትና የተሰቃዩት ሸዋ ሮቢት ነው።" የሚሉት አቶ ጌታቸው በሃገሪቱ የተለያየ ስፍራ ያሉ እንዲህ አይነት ማሰቃያዎች በአጠቃላይ መዘጋት አለባቸው ይላሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ማህበራዊ ድረ-ገፅ

ለዶ/ር አወል የፖለቲካ እስረኞች እነማናቸው የሚለውን የሚወስነው መንግሥት ነው።

"አሳሪም ፈቺም እሱ ስለሆነ እዚያ ምደባ ውስጥ የሚወድቁትን ራሳቸው ናቸው የሚወስኑት። "

የፖለቲካ እስረኛ ብያኔ ሰፊ ነው የሚሉት ዶ/ር አወል "የፖለቲከኛ እስረኛ የምንለው ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች የሚሳተፍና መንግሥት ያንን ግለሰብ ከፖለቲካ ምህዳር ውጭ ለማድረግ የተከሰሰ እና የታሰረ እንደሆነ ነው። ከዚህ ተነስተን ታዲያ እኒህ ሰዎች ሁሉ ይፈታሉ የሚለውን በሂደት የምናየው ነው" ይላሉ።

ዶ/ር አወል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ድረገፅ በተደጋጋሚ መታረም ከዚህ አንፃር ተግባራዊ ልዩነት የሚያመጣ አይመስላቸውም፤ ''ዋናው መለቀቃቸው ነው'' ይላሉ።

ለአቶ ጌታቸው መንግሥት እስረኞች መኖራቸውን ማመኑ ጥሩ ቢሆንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ገፅ ላይ የፖለቲካ እስረኞች ላለማለት ተደጋጋሚ ማስተካከያ መደረጉን በጥርጣሬ ይመለከተዋል።

መጀመሪያ ይነገር የነበረው እና በኋላ ላይ የሰማነው የተለያየ መሆኑ ራሱ አጠራጣሪ ነው ይላል። "በዚህ አገር የፀረ-ሽብር አዋጁ ራሱ አንዱ የፖለቲካ መሳሪያ ነው። ለኔ በዚህ አዋጅ የታሰሩ ሰዎች የፖለቲካ እስረኞች ናቸው።"

ከ1500 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ እስረኞች አሉ የሚለው አቶ ጌታቸው፤ የመንግሥት መግለጫ ግን እነዚህን ሁሉ ያካትታል ብዬ አላስብም ሲል ያስረዳል። ይልቁንም ይህንን ጉዳይ ለማስተንፈሻ ይሆናል ብለው ከሚያወጧቸው ነገሮች መካከል እንደ አንዱ ነው የሚመለከተው። " ቃላቸውን ያከብራሉ ብዬ አላስብም" ይላል።

ምን ይጠብቃሉ?

ዶ/ር አወል ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ፣ ፌደራላዊ ሥርዓቱ በትክክል ይስራ በማለታቸው ብቻ የታሰሩ ሰዎች የሚፈቱ ከሆነ ከአሁን በኋላ ሰዎች አመለካከታቸውን ስለገለፁ ብቻ መታሰራቸው ይቆማል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

አቶ ጌታቸው ደግሞ የፖለቲካ እስረኞች በአንዴ ይፈታሉ ብሎ አይጠብቅም። "ከዚህ በፊት ካለው ልምድም ስናይ ቀስ እያሉ ይፈቱ ይሆናል እንጂ፤ ጠንቅቆ የሚያቃቸውን የለውጥ ኃይሎች በአንዴ መፍታት የሚፈልጉ አይመስለኝም" ይላል።

ዶ/ር አዎል ግን ከእስረኞቹ መፈታት በተጨማሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ ደጋፊዎቻቸውን የሚያደራጁበት፣ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት የሚሰሩበት፣ ፍርድ ቤቶች ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት የሚዳኙበት፣ የመንግሥት ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ፓርላማ እና ምርጫ ቦርድ መስራት ያለባቸውን በአግባቡ የሚሰሩበት መንገድን ያበጃል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

አለምአቀፍ ተቋማት ምን አሉ?

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የእስረኞች መፈታትና የማዕከላዊ መዘጋት ዜና እንደተሰማ የኢትዮጵያ አጥኚውን ፍሰሃ ተክሌን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ ''ዜናው የአስከፊው የጭቆና ዘመን ማብቃት ምልክት ሊሆን ይችላል። በፖለቲካዊ ምክንያቶችና በሃሰት በተቀነባበሩ ክሶች ዓመታትን በእስር ላሳለፉ እስረኞች ግን እጅጉን የዘገየ ነው'' ብሏል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ታሳሪዎቹን በመልቀቅ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉት እንጠይቃለን። በተጨማሪም መንግሥት የፀረ-ሽብር ሕጉን ጨምሮ ለእስሩ ምክንያት የሆኑትን ሌሎች ጨቋኝ ሕጎች እንዲሰርዝ ካልሆነም በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል አለበትም ብሏል።

"የማዕከላዊ እስር ቤት መዘጋት እዚያ የተፈፀሙትን አሰቃቂ ድረጊቶች መሸፈኛ መሆን የለበትም። ማዕከላዊ ለዓመታት ሰላማዊ ተቃውሞን ባሰሙ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት አሰቃቂ ምርመራ የተካሄደበት የሰቆቃ ማዕከል ነው።

ስለዚህም አዲስ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ምዕራፍን መጀመር የሚቻለው ተፈፀሙ የተባሉት ሁሉም ሰቆቃዎችና የከፉ አያያዞች ምርመራ ተደርጎባቸው ፈፃሚዎቹ ለፍርድ ሲቀርቡ ብቻ ነው።'' የሚለው አምነስቲ ''የት እንደደረሱ ያልታወቁ ሰዎች እጣ ፈንታ ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ የተወሰኑ ሰላማዊ ተቃውሞ ያሰሙ እስረኞችን መልቀቅ ብቻውን በቂ አይደለም'' ብሏል።

''ምንም እንኳን መንግሥት ውሳኔውን እንዴትና መቼ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ባያሳውቅም ለረጅም ጊዜ የቆየውን ፖለቲካዊ ጭቆና ለማብቃት ወሳኝ እርምጃ ነው።'' ያለው ደግሞ ሂዩማን ራይትስ ዋች ነው።

ማዕከላዊ ተዘግቶ ታሳሪዎቹ ወደሌላ ቦታ የሚዘዋወሩ ከሆነና ተመሳሳይ ስቃይ ሚገጥማቸው ከሆነ ውሳኔው ትርጉም የለሽ ይሆናል የሚለው ተቋሙ፤ መንግሥት በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ የደህንነት ሃላፊዎች እስረኞችን ማሰቃየት የተከለከለና የሚያስቀጣ መሆኑን መንገር አለበት።

ሂውማን ራይትስ ዋች ጨምሮም መንግሥት በቀጣይ ሰላማዊ ተቃውሞን መፍቀድና ጨቋኝ ህጎችን በማሻሻል ተጨማሪ ለውጦችን በማድረግ ይኖርበታል ብሏል።

በተመሳሳይም በዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በማቆም ከውጪ የሚተላለፉ የሬዲዮና የቴሌቪዥን እንዲሁም የኢንተርኔ አገልግሎትን ማገዱን እንዲተው ሂውማን ራይትስ ዋች ጠይቋል።

የፖለቲካ እስረኛ ማን ነው?

ቁርጡ ያልታወቀው የታሳሪ ቤተሰቦች ጥበቃ

ተያያዥ ርዕሶች