ኢኮኖሚያዊ ተቃውሞና ያስከተለው ውጤት

ሰላም ባስ እና ዳሸን ቢራ Image copyright Selama and Dashen Facebook

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተነሳው ተቃውሞ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተቋማትን ምርቶችንና አገልግሎቶችን አለመጠቀም እንዲሁም የማጥቃት ሁኔታን አስተናግዷል።

በአገሪቷ መንግሥት በብቸኝነት በሚቆጣጠራቸው እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም አይነት ተቋም ባሉበት ሁኔታ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ከፍተኛ ቀጣሪ በሆነበት ሀገር ምርትና አገልግሎትን ላለመጠቀም አድማ መምታት (ቦይኮት ማድረግ) የተወሳሰበ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

በተቃራኒውም መንግሥት ህዝቡን መፈናፈኛ በማሳጣቱና ለሚነሱ ተቃውሞዎችም አፀፋዊ ምላሹ ሀይል በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ተቃውሞ እንደ አንድ ተፅእኖ መፍጠሪያ መንገድ እንደሆነ የሚናገሩም አሉ።

ቀዳሚ ኢላማዎች

በባለፈው ዓመት በባህርዳር ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ ብዙዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው። የክልሉ መንግሥት አፀፋዊ ምላሽን በመቃወም እንዲሁም ለሕይወት መጥፋቱ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባቸዋል የሚሏቸው ድርጅቶችን ያለመገልገል አድማ ታይቷል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በጥረት ኢንዶውመንት ፈንድና የእንግሊዙ ቫሳሪ ግሎባል ባለቤትነት የሚተዳደረው "ዳሽን ቢራ" አንዱ ነው።

የባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው አበበ ሰጠኝ 'ዳሽን ቢራን' ከማይጠጡት መካከል አንዱ ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሳው በባህርዳር ከተማ ከነበረ ተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ ነው።

በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ከተማ በርካታ ሰው የዳሽን ቢራን ፈፅሞ እንደማይጠጣ የሚናገረው አበበ በአንዳንድ መጠጥ ቤቶችም ከራሳቸው አልፈው ሌሎች ሲጠጡ ቢታዩ ከቁጣ አልፎ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ይገልፃል።

ለዳሽን ቢራ የገብስ አቅርቦት የሚሰጡትን ገበሬዎች ይህ አካሄድ ሊጎዳ እንደሚችል ቢያስብም "ለድሃ ህዝብ ምንም አማራጭ የለም፤ ባለው ነው የሚያምፀው፤ የዳሽን ቢራ ምርት በቀነሰ ቁጥር ገበሬው እንደሚጎዳ እናውቃለን ግን መንግሥትን ማስጠንቀቂያ መንገድ ነው" ይላል።

ሌላኛው የዚህ አይነት እርምጃ ተጠቂ በትግራይ ልማት ማህበር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ሰላም የአውቶብስ አገልግሎት ማህበር አንዱ ነው።

አሁን ከልማት ማህበሩ ወጥቶ እንደ አክሲዮን ማህበር በ1600 ባለድርሻዎች እንደተቋቋመ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሃጎስ አባይ ይናገራሉ።

ምን ገጠማቸው?

በቅርቡ ወደ ቁልቢ ገብርኤል በመጓዝ ላይ የነበሩ አራት የሰላም አውቶብሶች ተቃውሟቸውን በሚገልፁ ሰዎች መስታወቶቻቸው እንደተሰበረ አቶ ሃጎስ ያስታውሳሉ። ቀደም ባለው ጊዜም በተለያዩ ቦታዎች ጥቃትም ሁለት አውቶብሶች ተቃጥለዋል።

አቶ ሃጎስ ጥቃቱ ሰላም ባስ ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም ቢሉም የተለያዩ ሰዎች አስተያየት ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው። በርካቶች በሰላም አውቶብስ ለመሄድ ፍራቻ ላይ ናቸው።

"የሰላም ባስ አክሲዮን ማህበር ራሱን የቻለ ከመንግሥት ነፃ የሆነ የባለድርሻ አካላት ስብስብ ነው፤ በብዙዎች ዘንድ ግን የመንግሥት ተቋም እንደሆነ ተደርጎ መታየቱ የግንዛቤ እጥረት ነው" ይላሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ከ17 መሥመሮች ውስጥ አራት መሥመሮች በሀረር፣ በድሬዳዋ፣ ጂጂጋና አሶሳ ከሦስት ወራቶች በላይ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

"ከእነዚህ አራት መስመሮች ውጭ ከፍተኛ የሆነ ተፅእኖ አልገጠመንም። በማህበራዊ ድረ-ገፆች የሚወሩት እውነት ነው ከፍተኛ ተፅእኖ ያመጣሉ። ግን የባለፈው ዓመት ገቢ ጋር ስናስተያየው ከመቶ ሺ ብር በላይ ልዩነት የለውም'' አቶ ሃጎስ ይላሉ።

የዳሽን ቢራ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሙሉጌታ ማሩ በበኩላቸው የዳሽን ግማሹ ንብረት የአማራ ክልል መንግሥት ኢንዶውመንት ፈንድ የሆነው ጥረት በመሆኑ ብዙዎች መንግሥትን ለመቃወም ቢራውን መጠጣት እንዳቆሙ ይናገራሉ።

"በተደጋጋሚ ብዙዎች የሚያነሱት ይህ የጥይት መግዣ ነው የሚሉ አሉ። ግን የትኛው ድርጅት ነው ግብር የማይከፍለው? ይህ ድርጅት ከፖለቲካው ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም" የሚሉት አቶ ሙሉጌታ ለብዙ ወጣቶችም ሥራ እድል ፈጥሯል ይላሉ።

በዚህም ምክንያት ባህርዳር ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ደርሶብናልም የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ኪሳራ ላይ እንዳልሆኑ ነገር ግን ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲወዳደር ትርፋቸው በእንደቀነሰ ይናገራሉ።

"በባህርዳር አንዳንድ መጠጥ ቤቶች በሌሎች መብት በመግባት የሚያስፈራሩም አሉ" በማለት ይናገራሉ። በተለይም ባህርዳር ላይ ከሞቱት ሰዎችም ጋር ተያይዞ ሁኔታዎች ቀውስ እንደፈጠሩ አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ።

"በድሃ ሀገር ድርጅቶች ወይም ኢንቨስትመንቶች ቢከስሩ የበለጠ የሚጎዳው የሰራተኛው ክፍል ነው'' በማለት የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ ሥርዓቱን መቃወም መብት ቢሆንም የሰዎችን መብት የሚነካና ኢኮኖሚውን የሚያደናቅፍ መሆን ግን የለበትም።

አድማ እንደ ፖለቲካዊ ስትራቴጂ?

"አንድን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቃወም ወይም ጫና ለመፍጠር የተቋማትን ምርትና አገልግሎት አለመጠቀም ሊሆን ይችላል፤ ሁለተኛው ደግሞ በሚገለገለው ማህበረሰብ ውስጥ ጥሩ ምስል እንዳይኖራቸውና ደህንነት እንዳይሰማቸው ማድረግ ነው" በማለት የፓለቲካ ሳይንስ ተንታኟ ህሊና አማረ ትናገራለች።

የሚቃወመው ህዝብ ያለውን ሁኔታ በመገምገም ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው የምትለው ህሊና ትክክለኛ መሰረት አለው ወይስ የለውም ለሚለው ጥያቄ መልስ ላይኖረው ይችላል ወይም ከፍተኛ ጥናት ሊፈልግ ይችላል።

"ተቃውሞ ከሰማይ አይወርድም። ማህበረሰቡ ፓለቲካውን የተረዳበትን ሁኔታና ለዚያ እየሰጠ ያለውን ምላሽ አድማው ያሳያል። የኢኮኖሚ ግብአቶች ከፖለቲካ ጋር ተሳስረው ላይታዩ ይችላሉ። ያለው የየዕለት ኑሮ ወደ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲያመራ እነዚህ ስፍራዎችም ሆኑ ሁኔታዎች የፖለቲካ ስፍራ ይሆናሉ" ትላለች።

አንዳንዶች አድማውን ወይም ጥቃቱን ሃገሪቱ ላይ እንደተፈጠረ ቀውስ ወይም የሽብር ሁኔታ ቢያዩትም በተቃራኒው ለህሊና "ሰዎች አንድን ሥርዓት ልክ አይደለህም ለማለት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነው። የተቃውሞው ዋና መሰረት መንግሥት ራሱ ህብረተሰቡ እንደ የፖለቲካ መሳሪያነት እያያቸው ያሉትን አድማዎች ከማውገዝና ከማዳፈን ይልቅ ከህብረተሰቡ ጋር በጥልቅ ሊወያይ ይገባል" ትላለች።

ሕዝቡ ቅሬታውን የሚሰማበት መድረክ ከሌለ እንደዚህ አይነት ተቃውሞዎች እንደሚያይሉም ትገልፃለች። "የኢኮኖሚ ውድቀት ያመጣል ከዚያም በተጨማሪ ባለሀብቶች መንግሥትንና ህብረሰተሰቡን እንደሚያገለግሉ ሳይሆን እንደ ጠላት እንዲታዩ ያደርጋል" ትላለች።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ለክስተቶች ከውግዘት ይልቅ ፓለቲካዊ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል የምትለው ህሊና "ማውገዝ የቤተ-ክርስቲያን ሥራ እንጂ የፖለቲካ ሥራ አይደለም" ትላለች።

እነዚህ ክስተቶች ዘላቂ የሆኑ ተቃውሞዎች ሳይሆኑ ''ህዝቡ ያለውን ጥያቄ፣ መሰላቸትና መናድድን የሚያሳዩ ናቸው። ንግግሮች፣ ፅሁፎች ያላመጡትን ለውጦችም ማምጣት ይችላሉ" በማለት ህሊና ትገልፃለች።

መፍትሄውም መንግሥት ህዝቡ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ፈጥሮ በየአካካባቢው ችግሮችን በመቅረፍ ማሳየት አለበት ትላለች። ይህ ካልሆነ ግን ግጭቶች፣ መጠላላት ወይም ጥቃት መድረሱ ሊቀጥል እንደሚችልም ብዙዎች ይናገራሉ።