በፌስቡክ ማስታወቂያ የተሳካ ጋብቻ

ሶፊ ሊጆማ እና ቺዲማ አዴሙ Image copyright CHIDIMMA AMEDU

የፌስቡክ ተጠቃሚ ከሆኑ እስከዛሬ የተለየ ፖስት ሳያጋጥምዎ አይቀርም። ያልተጠበቀ የጓደኝነት ጥያቄ ቀርቦልዎት ወይም ከአንድ መልዕክት ጋር ስምዎ ተያይዞ (ታግ) ተደርገው ያውቁ ይሆናል። የማይፈልጉት ፎቶ በጓደኞችዎ ተለጥፎቦዎትም ይሆናል።

አንድ ናይጄሪያዊ ያደረገው ግን ፍፁም የተለየ ነው። ቺዲማ አዴሙ ታህሳስ 21 ቀን ልታገባው የምትፈልግ ሴት ካለች ምላሽ እንድትሰጠው ፍላጎቱን ፌስቡክ ላይ አሰፈረ።

የሚፈልጋት አይነት ሴት ከመጣች ምንም ጊዜ ሳያጠፋ እንደሚያገባት፣ ጋብቻው የሚፈፀምበትን እንዲሁም የሚስት ፍለጋ ማስታወቂያው የሚያበቃበትን ቀን ሁሉ በዝርዝር አስቀምጦ ነበር።

ናይጄሪያዊው በርካታ ምላሾችን ያገኘ ሲሆን ሶፊ ሊጆማ የተባለች ሴት ምላሽ ግን ትኩረቱን ሳበው። ለእሱ ፌስቡክ ፖስት 'ላገባህ እፈልጋለው' የሚል መልስ ሰጠች።

እሷ መጀመሪያ ነገሩን እንደቀልድ ነበር ያየችው። ነገር ግን ከናይጄሪያዊው ያገኘችው የፌስቡክ የውስጥ መልዕክትና ስልክ ህይወቷን ቀየረው።

በስልክ በተነጋገሩ በሁለተኛው ቀን ከአቡጃ ተነስቶ 500 ኪሎ ሜትር እሷ ወደ ምትኖርበት ምሥራቃዊ ናይጄሪያ ተጓዘ።

ከአንድ መደብር በር ላይ ቆማ ነበር የጠበቀችው። ነገሩ እንደተያዩ በፍቅር መውደቅ የሚባለው አይነት እንደሆነ ሶፊ ታስታውሳለች።

ከምታውቃቸው ወንዶች ሁሉ እሱ በጣም መልከ መልካም እንደሆነ ትናገራለች። ለሁለት ሰዓት ያህል ከተነጋገሩ በኋላ እዚያው አካባቢ ይኖር የነበረ አጎቱ ጋር እንዲሄዱ ጠየቃት።

ለአጎቱ ሊያገባት የሚፈልጋት ሴት እሷ እንደሆነች ነገራቸው። አጎቱም ይሁንታቸውን ገለፁ። እንደ ቺዲማ ሁሉ መላ ቤተሰቡ ጊዜ ማጥፋት አልፈለገም።

ቺዲማ በመጣበት ኢግቦ ባህል መሰረት ለጋብቻ የቤተሰብ ይሁንታ ወሳኝ ነው። ለፌስቡክ ማስታወቂያው መልስ በሰጠች በስድስት ቀን ውስጥ ተጋቡ።

በፌስ ቡክ ተገናኙ በባህላቸው መሰረት ተጋቡ። ባህልና ቴክኖሎጂ ሲገጣጠሙ ማለት እንዲህ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች