ዶ/ር መረራ ጉዲና ተለቀቁ

ዶ/ር መራራ ከእስር ተለቀው ወደቤታቸው መግባታቸውን በማስመልከት ደጋፊዎች ቲሸርት በማሰራት እና በመልበስ ጎዳና ላይ ወጥተው ነበር

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ዛሬ ከእስር ሲፈቱ "ከ400 ቀናት በኋላ በሰላም ከእስር በመለቀቄ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። እንደምታየው ሰዎች በድምቀት ተቀብለውኛል" ሲሉ ለቢቢሲው ኢማኑኤል ኢጉንዛ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለቢቢሲ ''ዶ/ር መረራ ነጻ ወጥተዋል'' ሲሉ ተናግረዋል።

የዶ/ር መረራ የቤተሰብ አባላትና ወዳጆቻቸው መረራን ለመቀበል ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ያቀኑት በማለዳ ቢሆንም፤ የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ግን ራሳቸው አሸዋ ሜዳ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንደሚወስዷቸው በመግለጽ እዚያው እንዲጠብቁ ነግረዋቸዋል።

ደጋፊዎቹም ''እስር እና እንግልት የኦሮሞን ትግል ወደኋላ አይመልሰውም'' የሚል መልዕክት የያዙ ጽሑፎችን በመያዝ እና የዶ/ር መረራ ምስል የታተመበትን ቲሸርት በመልበስ በቤታቸው አቅራቢያ እየጠበቋቸው ነበር።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ዶ/ር መረራ መኖሪያ ቤታቸው ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከየት ወዴት?

ዶ/ር መረራ ጉዲና መንግሥትን መቃወም የጀመሩት አምቦ ውስጥ የሁለተኛ ደራጃ ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ነበር። ከዚያም የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት እንዲወድቅ ምክንያት የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥም ተሳታፊ ነበሩ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖሊቲካል ሳይንስ ተማሪ በነበሩበት ጊዜም የመንግሥቱ ኃይለማሪያምን ወታደራዊ አስተዳደር በመቃወም ቅስቀሳዎችን ያካሂዱ ነበረ። በዚህም ሳቢያ ያለክስ ለሰባት ዓመታት በእስር ቤት ቆይተዋል።

ከእስር ቤት እንደተለቀቁም ካይሮ በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርት ለመቀጠል ወደ ግብፅ ተጓዙ።

በመለስ ዜናዊ የሚመራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ወታደራዊውን የመንግሥቱ ኃይለማሪያም አስተዳደር በማሸነፍ ሥልጣን ከያዘ ከአምስት ዓመታት በኋላ፤ መረራ ጉዲና የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) የተባለ ፓርቲ አደራጅተው ወደ ፖሊቲካው መድረክ ተመለሱ።

መረራ ጉዲና የመሰረቱት አዲሱ የኦሮሞ ፓርቲ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ቁጥር ያለውን የኦሮሞ ብሄር በራስ የመወሰን መብቱ እንዲከበርለት ማድረግ ነው።

በተጨማሪም ፓርቲው የኦሮምኛ ቋንቋ ከአማርኛ ጎን ለጎን የሃገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ፍላጎት አለው።

ይህ በመረራ ጉዲና ይመራ የነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ስያሜ ከፓርቲው ለወጡ አባላት በ2000 ዓ.ም በመሰጠቱ የኦሮሞ ሕዝቦች ኮንግረስ (ኦሕኮ) በሚል አዲስ ስም ፓርቲያቸውን መልሰው አዋቀሩ።

ዶ/ር መረራ ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን ሃገራዊ ትብብርን ለመፍጠር ''ኅብረት'' እና ''መድረክ'' የተባሉትን ትልልቅ የተቃዋሚዎች ስብስብ በማደራጀትና በመምራትም ከፍ ያለ ሚና ነበራቸው።

ዶ/ር መረራ ከፖለቲካው ጎን ለጎን የሃገሪቱ አንጋፋና ትልቁ በሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነትና በትምህርት ክፍል ተጠሪነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።

ዶ/ር መረራ በተለያዩ ጊዜያት ለምክር ቤት አባልነት እጩ ሆነው የተወዳደሩ ሲሆን፤ አወዛጋቢና ግጭቶችን አስከትሎ በነበረው የ1997ቱ ምርጫ በትውልድ አካባቢያቸው ተወዳድረው በማሸነፍ ለአምስት ዓመታት በምክር ቤት አባልነት ቆይተዋል።

ዶክተር መረራ የመሰረቱትና ለዓመታት ሲመሩት የቆየው የኦሮሞ ሕዝቦች ኮንግረስ (ኦሕኮ) ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመጣመር ጠንካራና በኦሮሚያ ክልል ብሎም በመላው ሃገሪቱ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ፓርቲ እንዲመሰረት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ፤ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ጋር ፓርቲያቸውን በማዋሃድ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እንዲመሰረት አድርገዋል።

በ2008 ዓ.ም በተለይ በኦሮሚያና በአማራ አካባቢዎች ተቀስቅሶ ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ ''ከፀረ-ሠላም'' እና ''ከሽብር'' ቡድኖች ጋር ግንኙነት በማድረግ ለእስር መዳረጋቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ዶክትር መረራ በፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪነታቸውና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ለዓመታት ባካበቱት እውቀትና ልምድ ስለኢትዮጵያ የተለያዩ ፅሁፎችንና ንግግሮችን እንዲያቀርቡ በተለያዩ መድረኮች በአስረጂነት ይጋበዛሉ።

ከነዚህም መካከል እስር ቤት ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ጥቅምት 30/2009 ዓ.ም በአውሮፓ ፓርላማ ተገኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ባደረጉት ንግግር በመንግሥት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተችተው ነበረ።

አጭር የምስል መግለጫ ደጋፊዎቻቸው ''እስር እና እንግልት የኦሮሞን ትግል ወደኋላ አይመልሰውም'' የሚል መልዕክት የታተመበት ባነር ይዘው እየጠበቋቸው ነው

በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ምስሎች ላይ በሃገሪቱ ፓርላማ አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን መሪ ከሆኑት ዶክትር ብርሃኑ ነጋ ጎን ተቀምጠው መታየታቸውን አንዳንዶች ለእስራቸው እንደተጨማሪ ምክንያት ያነሳሉ።

ክስ

ዶክተር መረራ ከአውሮፓ መልስ ለእስር ከተዳረጉ በኋላ፤ በኦሮሚያ ሁከት እንዲከሰትና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ጥሪ አስተላልፈዋል በሚል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሰርቶባቸዋል።

ዶክተር መረራ የቀረቡባቸው ክሶች

  • የኦፌኮ አመራርነታቸውን እና የፖለቲካ ድርጅቱን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የፖለቲካዊ፣ የሃይማኖታዊ ወይም የአይዶሎጂ አላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተፅዕኖን በማሳደር የሃገሪቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማናጋትና ለማፈራረስ በማቀድ ተቀሳቅሰዋል" ይላል የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ።
  • በ2006 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማና የፌንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላንን ተከትሎ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ደጋፊዎቻቸውን ሁከትና ብጥብጥ እንዲቀሰቀሱ እንዳደረጉ
  • በምዕራብ ሸዋ ዞን የአምቦ ካራ የመንገድ ግንባታ በመቆራረጥ፣ ካምፕ በማቃጠል፣ በተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ላይ ከ2 ሚሊየን 957 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት እንዲወድም በማስደረግ
  • በቡራዩ ከተማ ከ42 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ንብረቶች ላይ ጉዳት እና ውድመት እንዲደርስ በማስደረግ፤ በደቡብ ምዕራብ ሽዋ ዞን ወሊሶ፣ አመያ፣ ጎሮ፣ ቶሌ፣ ኢሉ፣ ቀርሳ፣ ወንጪ ወረዳዎች ግምታቸው ከ17 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆኑ በቀበሌ መስተዳደር፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ በኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩ የአበባ ድርጆቶች፣ የአትክልት ማምረቻ እና የተለያዩ ንብረቶች እንዲወድሙ እና ጉዳት እንዲደርስ አስደርገዋል።
  • በመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም በኢሬቻ አከባበር ስነ ስርአት ላይ የመንግስት ታጣቂዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ በወሰዱት ግድያ 678 ሰዎች ተገድለዋል በማለት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሁከት ጥሪ ማስተላለፋቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ