የኢህአዲግ ፖለቲከኞችን የመፍታት አንድምታ

ደ/ር መረራ ጉዲና ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ
አጭር የምስል መግለጫ ዶ/ር መረራ ጉዲና

እንደ ኢትዮ ትራያል ትራከር ድረገፅ መረጃ ከሆነ በአሁን ሰአት በፀረ ሽብር ሕጉ ተከሰው ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተለያዩ ችሎቶች እየታየ ያለ ከ900 በላይ ሰዎች ይገኛሉ።

እነዚህ ግለሰቦች ከግንቦት 7፣ ከኦነግ እና ሌሎች በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር አብራችኋል በሚል የተከሰሱ መሆናቸውን ድረገፁ ላይ የሰፈረው መረጃ ያሳያል።

በሀገሪቱ ከሶስት አመት በላይ በዘለቀው ተቃውሞ ምክንያት መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል ከገባ በኋላ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ 115 በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ሥር የሚገኙ 413 ደግሞ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ስር ያሉ እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ ይለቀቃሉ ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ክሳቸው የሚቋረጠው እና ይቅርታ የሚደረግለቸው በጸረ-ሽብር ህጉ የተከሰሱትንም ይጨምራል ብለው ነበር።

ይህንን ተከትሎም ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች ተለቀዋል። የእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት መለቀቅ በርግጥ ኢህአዴግ እንዳለው የፖለቲካውን ምህዳር ያሰፋል? የተሻለ መግባባትስ ይፈጥራል ስንል ምሁራንን አረናግረናል።

ዶ/ር አሰፋ ፍሰሃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። ይህ የመንግስት ውሳኔ ያለውን አንድምታ ሲያስረዱ፤ ለበርካታ ዓመታት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ መሪዎቹ እስር ቤት ተቀምጠው የተሻለ መግባባት መፍጠር እና ከህዝብም ጋር ለመነጋገር አስቸጋሪ መሆኑን መንግሥት ተረድቷል ይላሉ።

"መንግሥት አሁን የወሰደው እርምጃ ባለፈው ሃያ አምስት አመታት ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርአት በኢትዮጵያ የሚፈልገውን ያክል ስላልሄደ ነው። በተቃዋሚዎችም ሆነ በመንግስት በራሱ ችግር ውጤቱ አስደሳች አልነበረም።"

ስለዚህ የተሻለ የመድብለ ስርአት እና የተሻለ መግባባት መፍጠር እንዲቻል እነዚህን መሪዎች መፍታት የግድ ነው ብለዋል።

ላለፉት ሶስት ዓመታት ሕዝቡ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ሲጠይቁ ነበር የሚለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆነው ኩማ በቀለ፤ ''መንግሥት እስረኞቹን የፈታው ለታሳሪዎቹ ፍቅር ኖሮት ሳይሆን ህዝቡ ከፍተኛ ጫና ስላሳደረበት ነው' ይላል።

ከባለፉት 26 ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ፖለቲካዊ ምክንያቶች የታሰሩት ዜጎች ቁጥር ወደ አንድ መቶ ሺህ ይጠጋል የሚሉት ደግሞ የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ሰኚ ናቸው። ዶ/ር ብርሃነ፤ ይህን ያክል የፖለቲካ እስረኛ በሃገሪቱ ውስጥ እያለ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታት ''በህዝብ እንደ መቀለድ ነው'' ይላሉ።

የፖለቲካ አመራሮችን እና አባላትን በመፍታት ብቻ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል ብለው የማያምኑት ዶ/ር አሰፋ ፍሰሃ ቀሪዎቹን ችግሮች ለመፍታት ግን የመጀመሪያ ጥሩ እርምጃ ነው ብለዋል።

አቶ ነፃነት በላይ በአምንስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ የጥናት እና አድቮኬሲ ዳይሬክተር ናቸው። ድርጅታቸው የእነዶ/ር መረራን መለቀቅ ተከትሎ መግለጫ አውጥቷል።

አቶ ነፃነት ስለመግለጫው ይዘት ሲያብረሩ "የተወሰኑ እስረኞች መፈታት ጥሩ እርምጃ ነው። ነገር ግን በርካታ የሕሊና እስረኞች አሁንም በእስር ቤት ታስረው፣ ተፈርዶባቸው አልያም የፍርድ ሂደታቸውን የሚከታተሉ አሉ፤ ስለዚህ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ አለባቸው የሚል መልዕክት በመግለጫው ላይ ተላልፏል ብለዋል።

አቶ ነፃነት የመንግስት ባለስልጣናትም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ በተለያየ ፖለቲካዊ ምክንያት ሰዎች እንዳይታሰሩ የማረጋገጫ መፍትሔ መውሰድ አለባቸውም ይላሉ።

እንደ አቶ ነፃነት ለዚህም የሚረዳው ደግሞ እንደ ፀረ ሽብር ሕጉ ያሉ ለበርካታ ሰዎች መታሰር ምክንያት የሆኑ ሕጎች በአስቸኳይ በሕዝብ እንደራሴው ቀርበው አስፈላጊው ማሻሻያ ሲደረግባቸው ነው።

ምህዳሩን ስፋት

''በመጀመሪያ ደረጃ የህዝቡ ጥያቄ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ሳይሆን ስልጣንን ከመንግሥት ወደ ህዝብ ይሸጋገር ነው። መንግሥት የህዝቡን ጥያቄ የተረዳበት ሁኔታ በራሱ ትክክል አይደለም'' ሲሉ ዶ/ር ብርሃነ ያስረዳሉ።

ዜጎችን ያለአግባብ ለእስር የሚዳርጉ ህግ እና ስርዓቶች እስካልተሻሻሉ ድረስ፣ የመንግሥት ስራ አስፋጻሚ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እስካልተወጡ ድረስ እና የፍትህ አካላትም በራሳቸው የሚመሩ እስካልሆኑ ድረስ እስረኞችን በመፍታት ብቻ መንግሥት እንደሚለው የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት አይቻልም ሲሉ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ይሞግታሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሰዎች ሃሰባቸውን በነፃ በመግለፃቸው፣ በፖለቲካ ምህዳር ውስጥ በመሳተፋቸው ብቻ እስርና እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛል የሚሉት አቶ ነፃነት ደግሞ ይህንን በቃ ብሎ ማቆም ለሃገሪቷ መረጋጋት፣ ለዲሞክራሲ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ዋናው ነገር ግን ይህ እርምጃ ብዙዎችን ያጠቃለለ ነው ወይ የሚለው ነው የሚሉት አቶ ነፃነት "አሁንም ድረስ በእስር ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ያለአግባብ የታሰሩ ዜጎች አሉ፤ ስለዚህ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት ይገባቸዋል" ብለዋል።

"ከዚህም በተጨማሪ መንግስት አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ማሻሻያዎችን መውሰድ ይገባዋል። እንዲህ አይነት መዋቅራዊ ለውጦች ካልተወሰዱ ይህ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል።"

ሰዎች በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈው በነፃነት ሃሳባቸውን መግለፅ የሚችሉት እና የፖለቲካው ምህዳርም የሚሰፋው የዜጎች ሰብአዊ መብት ሲጠበቅ ነው የሚሉት አቶ ነፃነት እነዚህን የሰብዓዊ መብቶች ደግሞ ኢትዮጵያ መፈረሟን ያስታወሳሉ።

አቶ ነፃነት ኢትዮጵያ ይህንን ባላከበረችበት ዜጎች እታሰራለሁ እገደላለሁ ከሚል ፍራቻ ተላቀው ሃሳባቸውን በነፃነት ባልሰጡበት የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋል ብሎ መናገር ያስቸግራል ሲሉ ይሰጋሉ።

ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁን ከግለሰቦች ጋር ለሚኖረው ውይይት እና ንግግር እነዚህ መብቶች መጠበቅ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ