አለመግባባት ለማንም አዋጭ አይደለም

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አል አሲሲ Image copyright Office of the President (Egypt)

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግብጽ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አል ሲሲ ጋር ተገናኘተው ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቢቢሲ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳይ ጽ/ቤት ቅርበት ካላቸው ምንጮች መረዳት እንደቻለው፤ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ያቀኑት ከፕሬዝደንት አል ሲሲ ጋር ተገናኝተው በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ላይ ተወያይተው ልዩነቶችን ለማጥበብና ተቋርጦ የነበረውን ድርድር የሚቀጥልበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።

በግብጽ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይፋዊ የትዊተር ገጽ 6ኛው ዙር የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሚንስትሮች ጥምር የውይይት መድረክ ተጀምሯል በማለት ትምህርት፣ ጤና፣ የተፈጥሮ ሃብት እና ማዕድን የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ሲል አስፍሯል።

የግብጹ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ለአል አራሃም ኦንላይን እንደገለጹት፤ "ሁለቱም ሃገሮች ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ተጠቅመው የጋራ ጥቅማቸውን ለማስከበርና ለመተባበር ዝግጁ ናቸው" ብሏል።

"በናይል ተፋስስ ለተጀመረው የትብብር ድርድር ይህ ጉብኝት የተሳካ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ተስፋ አለኝ" ሲሉም ሳሚ ሽኩሪ አክለዋል።

አለመግባባት ለማንም አዋጭ አይደለም

ከጥቂናት ቀናት በፊት አብዱል ፈታ አል ሲሲ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር የግብጽን የውሃ ጥቅም እንደሚያስጠብቁ ቃል ገበተው ነበር። ''ሀገራችንን መከላከል የሚችል በቂ ወታደራዊ ኃይል አለን። ከማንም ጋር አናብርም፥ በሌላ ሃገር ጉዳይም ጣልቃ አንገባም" ብለው ነበር።

አል ሲሲ ግብፅ በአባይ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ቃል ገቡ

መቀመጫውን አሜሪካ ባደረገው የውጪ ጉዳዮች ካውንስል ውስጥ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ስቲቨ ኩክ፤ "የአባይ ወንዝ በግብጽ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሯል። ለሁሉም የሚበጀው ግን ውይይት እና መግባባት ላይ መድረስ ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

ስቲቨ ''ለኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ ግድቡ ትልቅ ፋይዳ አለው። ለሱዳን ደግሞ ወንዙ የግብርና ዘርፏን ለማሻሻል ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ለዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ከስምምነት ላይ በመድረስ የውሃ ድርሻዋን ከፍ ለማድረግ እየሰራች ነው። የሱዳን አካሄድ ደግሞ የግብጽን የውሃ ድርሻ ስለሚቀንሰው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መጥቷል'' ሲሉ ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ወደ ካይሮ ማቅናታቸው እና ውይይቶችን ማስቀጠላቸው መልካም ነገር ነው። ለሁሉም ሃገራት በአባይ ውሃ ጉዳይ አለመግባባት ውሰጥ መግባት ኪሳራ ነው የሚሆነው ይላሉ ስቲቨ ኩክ።

የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት ሁሉም ሃገራት የራሳቸው የሆነ የውስጥ ችግር አለባቸው። በአሁኑ ወቅት በግብጽ በሲናይ ባህረ ሰላጤ ከሰርጎ ገቦች ጋር እየተዋጋች ነው እንዲሁም በምዕራባዊ የግብጽ በረሃማው ክፍል ውስጥ የአሸባሪዎች ቡድን እንቅስቃሴዎች ይስተዋላሉ።

በኢትዮጵያም የፖለቲካ ውጥረት አለ፤ ስለዚህ ሃገራቱ በራሳቸው ላይ ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ከመጨመር ይልቅ መግባባት ላይ ቢደርሱ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ ያብራራሉ።

ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ በአፍሪቃ ቀንድ እየታየ ያለው ሁኔታ ሃገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እየወሰዱት ያለው እርምጃ እንጂ አዲስ ነገር የለውም ይላሉ።

ዶ/ር ያዕቆብ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ በአባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ዋነኛ ተዋናዮች እንዲሆኑ ሃሳብ ማቅረቧን አስታውሰው፤ በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ከሱዳን ተለይታ ወደ ግብፅ የምታደላበት ምንም ምክንያት ሊኖራት አይችልም ይላሉ። እንደ ዶ/ር ያዕቆብ ከሆነ ሶስቱም ሃገራት በጋራ ተስማምተው ሊሰሩ ይገባል።

ከአንድ ወር ገደማ በፊት የግብጹ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየው ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።

ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አዲስ ሃሳብ አቀረበች

ከውይይታቸው በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት "የግብፅ ሕዝብ ተቆጥቷል ባልልም ስጋት ላይ መውደቁን ግን መናገር እችላለሁ" ሲሉ ሳሚ ሹክሪ ተናግረው ነበር። አዲስ ምክረ ሃሳብም አቅርበው ነበር።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ግብጽ ያመጣችውን ምክረ-ሃሳብ ኢትዮጵያ እንደምትመለከተው ገልጸው ''በሁለቱም ሃገራት የሚቆጣ ሕዝብ አይኖርም። ኢትዮጵያም ግብፅን ለመጉዳት የምትሰራው ሥራም አይኖርም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ምክረ ሃሳቡ የዓለም ንግድ ባንክ በአባይ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቅ ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አል ሲሲ ይመክሩበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የሶስትዮሽ ውይይት

Image copyright OFFICE OF THE PRESIDENT EGYPT

የአባይ ወንዝ የጋራ አጠቃቀም በተመለከተ በአስሩ የተፋሰሱ አባል ሃገሮች ስምምነት የረቀቀው ሕግ በግብፅና በሱዳን እምቢተኝነት በስድስቱ ፈራሚነት ገዢ ሆኖ በፈራሚ ሃገሮች ምክርቤት በመፅደቅ ላይ ይገኛል።

ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ሶስቱም የተፋሰሱ ምስራቃዊ ክፍል ሃገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁኔታ በተመለከተ ለሶስት ዓመታት ያህል ያደረጉት ውይይት በተነሳው ውዝግብ ምክንያት ተቋርጧል መባሉ ተሰምቷል።

ይህንን ተከትሎ ነበር በተለይ በግብጹ ፕሬዝዳንት የተሰጡ አወዛጋቢ መግለጫዎች ሲያነጋግር የቆየው። በግብፅ የቀረበው አዲሱ ምክረ ሃሳብም ሱዳንን ያገለለ እንዳይሆን ስጋታቸውን የሚገልፁ ወገኖች አሉ።

ተያያዥ ርዕሶች