ወልዲያ ውስጥ 7 ስዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ

ወልዲያ ካርታ

በወልዲያ ከተማ በጥምቀት በዓል ማግስት ቅዳሜ ዕለት የተከበረው የቃና ዘገሊላ ክብረ በዓል ማብቂያ ላይ የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የሰባት ሰዎች ህይወት ሲጠፋ በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በበዓሉ ተሳታፊዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተከሰተው ግጭት አስለቃሽ ጭስና ጥይት እንደተተኮሰ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል::

ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በተከሰተው ግጭት ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካቶች የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞችና የሆስፒታል ምንጮች ገልፀዋል::

ነገር ግን የሟቾቹና የጉዳተኞቹ ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚበልጥ እየተነገረ ነው::

ከአዲስ አበባ 500 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው በወልዲያ ከተማ ቅዳሜ ዕለት ለተከሰተው ግጭት ምክንያት ነው ተብሎ ቢቢሲ ያናገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች የገለፁት፤ ወጣቶች በሚጨፍሩበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ለማስቆም በመሞከራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህን ሙከራ የተቃወሙ አንዳንድ ወጣቶች በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን ይህንን ተከትሎም ሕዝቡ ላይ የተኮሱት አስለቃሽ ጭስ ግርግሩን ማባባሱን ከዚያም ተከታታይ የጥይት ተኩስ እንደተሰማና ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል፡፡

የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ቅዳሜ ምሽት በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በወልዲያ ከተማ በወጣቶች እና በፀጥታ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ማልፉን አረጋግጠው ለንፁሀን ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑትን ለህግ ይቀርባሉ ብለዋል::

ግጭቱ ለሁለትኛ ቀን እሁድም ቀጥሎ በሰውና በንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳትን አስከትሏል:: በከተማዋ ያሉ የንግድ ተቋማት ተዘግተው የዋሉ ሲሆን መንግዶችም በተቆጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተዝግተው ከፀጥታ ኃይሎች ውጪ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ተገተው ነበር:: የተኩስ ድምፅም ከተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ይሰሙ እንደነበር ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እናት ለቢቢሲ ተናግረዋል::

ወልዲያ ውስጥ የአንድ ካፍቴሪያ ባለቤት ስሙን ሳይጠቅስ ለቢቢሲ እንደተናገረው እሁድ ዕለትም አልፎ አልፎ ከሚሰማው የተኩስ ድምፅ በተጨማሪ ጠዋት ላይ ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በድንጋይ ሲፋለሙ እንደነበር እማኝነቱን ስጥቷል::

በሰው ህይወትና አካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በእሳት የውደሙ ንብረቶች እንዳሉ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ገልፀዋል::

የአማራ ክልል ቴሌቪዥን እንደዘገቡው የሟቾች ቁጥር ሰባት ደርሷል:: ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ግን ቁጥሩ ከፍ እንደሚል ያምናሉ:: የካፍቴሪያው ባለቤት እንደሚናገረው "እኔ እንኳን የማውቀው አንድ ታታሪ ወጣት ተገድሏል" ብሏል::

እሁድ እለት ተቃውሞው ከወልዲያ ሃያ ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው አነስተኛ ከተማ ሀራ ተዛምቶ መንገድ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተነግሯል::

ተያያዥ ርዕሶች