የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት እርምጃ አሳስቦኛል አለ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ Image copyright UNMultimedia
አጭር የምስል መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ዛሬ በጄኔቫ ባወጡት መግለጫ የጸጥታ ኃይሎች የወሰዱት የኃይል እርምጃ እጅጉን አሳስቦናል አሉ።

ቃል አቀባይዋ እንዳሉት ባሳለፈነው ቅዳሜ እና እሁድ የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የጥምቀት በዓልን በሚያከብሩበት ወቅት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ አስታውሰዋል።

ወልዲያ ውስጥ 7 ስዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ

በወልድያ ከተማ የጸጥታ ኃይሎች ይህን እርምጃ የወሰዱት የበዓሉ ተሳታፊዎች ጸረ-መንግሥት ዝማሬዎችን በማሰማታቸው እነሱን ለማስቆም በወሰዱት እርመጃ ጉዳት መድረሱን በመግለጫቸው ያስታወሱት ቃል አቀባይዋ፤ ይህ ክስተት ኢህአዴግ ዘርፈ ብዙ ማሻሻዮችን አደርጋለሁ ባለ ማግስት መከሰቱ ያሳዝናል ብለዋል።

''የሃገሪቱ ባለስልጣናት፤ የጸጥታ አካላት ኃይልን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ሌሎች አማራጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ'' ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ራቪና ሻምዳሳኒ በመግለጫቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በሰጡት መግለጫ ''ህይወታቸውን ያጡና የተጎዱ መኖራቸውን ማረጋገጣቸውንና ፤ ክስተቱን በተመለከተ ''በጥንቃቄ እናጣራለን'' ማለታቸውን አስታውሰዋል።

አስቸኳይ የሆነ የማጣራት ሥራው ገለልተኛ እና አድልዎ በሌለው አካል ተካሂዶ ጥፋተኞች ከህግ ፊት እንዲቀርቡ ስንል እናሳስባለን ብለዋል በመግለጫቸው።

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት አስፈላጊ የሆኑ የሕግ እና ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና ስልጠናዎችን በመስጠት ሕግ አስከባሪዎች አለም አቀፍ ሕግጋቶችን ተከትለው እንዲሰሩ ማስቻል አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የፖለቲካ ውጥረት በነገሰባት ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት እርምጃ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ