ዶክተሩ ለፈፀመው ጥፋት 175 ዓመት ተፈረደበት

ዶክተር ናሳር Image copyright Reuters

የቀድሞው የአሜሪካ ጅምናስቲክ ቡድን ዶክተር ላሪ ናሳር ፆታዊ ጥቃት ፈፀሙ 160 በሚደርሱ በሴቶች ከተመሰከረበት በኋላ ከ40 እስከ 175 ዓመት የሚደርስ እስር ተፈረደበት።

ዶክተሩ ለፈፀመው ጥፋት ተፀፅቶ ይቅርታ ለመጠየቅ ቢሞክርም የችሎቱ ዳኛ ከልቡ አይደለም በሚል ቀሪ ዘመኑን በእስር ቤት እንዲያሳልፍ ወስነውበታል።

ናሳር የኦሊምፒክ ቡድን አባላትን ጨምሮ አስር ለሚደርሱ በልጃገረዶችና በወጣት ሴቶች ላይ ለተፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ብቻ ጥፋተናኛ መሆኑን ግን አምኗል።

የ54 ዓመቱ ዶክትር ከህፃናት ጋር የተያያዙ ህገ-ውጥ ምስሎችን ይዞ በመገኘቱ ቀደም ሲል የእስር ፍርድ ተላልፎበት ነበር።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ሮዝሜሪ አኩዊሊና ብይን በሰጡበት ጊዜ ለናሳር እንደነገሩት ''የጥቃትህ ሰለባዎችን ለመስማት እድሉን እንዳገኘሁት ሁሉ፤ አንተ ላይ ብይን ስሰጥ ክብር ይሰማኛል። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ከእስር ቤት ውጪ ለመኖር የሚፈቀድልህ ሰው አይደለህም'' ብለዋል።

በግለሰቡ ላይ ጠንከር ያሉት ዳኛዋ ጨምረውም ''የፈፀምከውን አላመንክም፤ እኔም ላምንህ አልችልም። ስለዚህ የመጨረሻውን የሞት ፍርድ ወስኛለሁ'' ብለዋል።

ለሰባት ቀናት በተሰማው የጥቃቱ ሰለባዎች በስሜት የተሞላ ምስክርነት በኋላ ናሳር ለፍርድ ቤቱ የሚለው ነገር ካለው ዕድል ተሰጥቶት ነበር።

''ከሳሾቼ ከተሰማቸው ህመም፣ ስቃይና የስሜት መጎዳት ጋር ሳነፃፅረው፤ ስለተፈፀመው ነገር የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን የሚገልፁልኝ ቃላት አላገኘሁም'' ሲል መፀፀቱን በታዳሚ ለተሞላው ፍርድ ቤት ተናግሮ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች