በአባይ ወንዝ ጉዳይ ጉብኝትና የአደራዳሪ ግብዣ

ዓባይ
አጭር የምስል መግለጫ የዓባይ ወንዝ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውሃ መጠን በኢትዮጵያ ከሚጥለው ዝናብ ያገኛል

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ግብፅ የተቋረጠው ድርድር ይቀጥል ዘንድ አዲስ መፍትሄን የያዘ ምክረ ሃሳብ ይፋ አድርገው ነበር።

ይህን ትልቅ መነጋገርያ ሆኖ የሰነበተው ምክረ ሃሳብ ግብፅ "ገለልተኛ" ያለችውን የዓለም ባንክ በመካከላቸው ገብቶ እንዲያግባባ የሚጠይቅ ነው።

ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በካይሮ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ለፕሬዝዳንት አል ሲሲ፤ ኢትዮጵያ ግብፅን የሚጎዳ ተግባር እንደማትፈፅም አረጋግጠዋል።

የግድቡ ግንባታ ከ65 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ግብፅ የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር አለመሳካቱና የግድቡ ግንባታ ወደ መጠናቀቁ መድረሱ ያሰጨነቃት መሆኑን የውኃ ተመራማሪው ይገልፃሉ።

የዓለም ባንክን ለምን

ኢትዮጵያ በአባይ ዙሪያ የምታካሂደውን የልማት ሥራን የዓለም ባንክ እንደማይደግፍ መንግሥት ደጋግሞ ይገልፃል። ኢትዮጵያ ለግድብና መሰል ሥራዎች ዕርዳታ እንዳታገኝ በባንኩ ውስጥ ያሉ የግብፅ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተፅዕኖ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

ለዚህም ነበር መንግሥት ይህንን በአፍሪካ ትልቁ የውኃ ግድብ በራሱ ወጪ ለመስራት ያቀደው።

የአባይ ውሃ ፖለቲካ ገለልተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አና ኢሊና ካስክኦ፤ የዓለም ባንክ የአደራዳሪነት ግብዣን አስመልክተው ለቢቢሲ እንደተናገሩት "እንደ አጠቃላይ መርህም ሆነ በህዳሴ ግድብ የመግባቢያ ሰነድ ላይ እንዳሰፈረዉ፤ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በድርድሩ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም አካላት ጋባዥነትና ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት" ይላሉ።

እንዲሁም ደግሞ ሃሳቡ የቀረበበትን ወቅት ጥያቄ ያነሱበታል "ሦስቱም አገሮች ላለፉት ሰባት ዓመታት ለብቻቸው ያደረጉት ድርድር ፍሬ አፍርቶ ከሆነ ለምን የመጨረሻውን ውጤት ተግባራዊ ማድረግ አቃታቸው?" በማለት ይጠይቃሉ።

በስዊድን አገር ሉንድ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ለዶክትሬት ድግሪው በአባይ ውሃ ዲፕሎማሲን በተመለከተ በማጥናት ላይ የሚገኘው አቶ ወንድወሰን ሚቻጎ ሰይድ እንደሚለው "የዓለም ባንክ በላይኛው የአባይ ተፋሰስ ላይ ግብፅ ላላፀደቀችው ፕሮጀክት ድጋፍ አይሰጥም። ይሄ ፍትሃዊነት የጎደለው ልማድ አሁን ተቀይሯል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዚህ ድርጅት ላይም ሆነ ገንዘቡ ላይ ፍላጎት የላትም" ይላል።

"ዓለም ባንክ ከአሁን በኋላ በናይል ጉዳይ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርግ አይቻለውም" በማለትም ይደመድማል።

አጭር የምስል መግለጫ የህዳሴው ግድብ ሰባት ጌጋ ዋት ኃይል ያመነጫል

ሱዳንን ገለል ለማድረግ

ግድቡ ላይ ሲካሄድ የቆየው ድርድር በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ነው። የጋራ ስምምነትም በሦስቱ አገራት መካከል ነበር። ነገር ግን ሱዳን በግድቡ ላይ ያላት አቋም ከግብፅ በተቃራኒ በመሆኑ፤ በዚህ ምክንያት በሁለቱም አገሮች መካከል ውጥረት ነግሷል።

ግብፅ ባቀረበችው ሃሳብ ድርድሩ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ እንዲሆን እና ሱዳን ከጨዋታው ውጪ እንድትሆን ጥያቄ ማቅረቧም ተሰምቷል።

ዶክተር አና ይህንን በተመለከተ "ግድቡ ላይ አሁን በመካሄድ ላይ ያለውም ሆነ ወደፊት የሚካሄድ ማንኛውም ድርድር የሦስትዮሽ መሆን አለበት። አንዳቸውንም ማግለል አይቻልም። በአባይ ውሃ ዙሪያ የሚደረግ ማንኛውም ድርድር በሁለት አገሮች መካከል የሚሆንበት ግዜ አብቅቷል" ይላሉ።

አቶ ወንድወሰን እንደሚለው ግን "ይሄ የግብፅ ጥያቄ ስትራቴጂካዊ አካሄድ ነው። ምክንያቱም ሱዳንን ከሂደቱ ለማስገለልና በሌላ አካል ለመተካት የሚደረግ ጥረት ነው" ይላል።

ግብፅ ዓለም ባንክን በመጋበዝ ጉዳዩ ከድርድር ወደ ግልግል እንዲሸጋገር እየስራች መሆኑንም ይናገራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ለቢቢሲ እንደገለፁት ''በግድቡ ላይ የሚካሄደው ማንኛውም ዓይነት ድርድር፤ ስምምነት ላይ ከተደረሰበት የጋራ መግባብያ መርህ ውጪ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት አይፈቅድም።''

የዓለም ባንክን በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግሥት አካሄዱን እንደማይቀበለው ገልፀው "ሦስቱም አገራት የሚወስኑት ጉዳይ ብቻ ይሆናል" ይላሉ። በጉዳዩ ላይ ሱዳንን ያገለለ ምንም ዓይነት አካሄድ ተቀባይነት እንድሌለው በመናገር።

የካይሮ ጉብኝት

አቶ መለስ ጉብኝቱ በግድቡ ዙርያ በሦስቱም ሃገሮች መካከል የተቋረጠው ድርድር እንዲቀጥል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይገልፃሉ።

ዶክተር አና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ያለውን ጠቀሜታ ሲጠቅሱ "የግድቡን ሙላት እና የወደፊት አሰራሩን በተመለከተ መነጋገር ማለት ሦስቱም ሃገሮች እንዴት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚቀይሩት መወያየት ማለት ነው" ይላሉ።

"የእኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ለዲፕሎሚሲና ለታይታ ይመስለኛል" የሚለው አቶ ወንድወሰን በቀይ ባሕር አካባቢ የተከሰተውን ውጥረት ለማርገብ ካልሆነ ግድቡን በተመለከተ ትርጉም ያለው ነገር እንደማይጠብቅ ይናገራል።

በህዳሴ ግድብ ዙርያ የሚነሱ ጉዳዮች ማለትም የውሃ መጠንና የመሙላት ሂደት እንዲሁም በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖን በተመለከተ ያለው ውዝግብ በነበረበት ይቀጥላል ባይ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ በበኩላቸው በጉብኝቱ ጠቃሚ ስምምነት ላይ መደረሱንና ''ግብፅ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንዱስትሪ ዞን እንድትገነባ መንግሥት አስፈላጊ የመሬትና መሰረተ-ልማትን እንደሚያቀርብ'' መስማማታቸውን በመግለፅ የጉብኝቱን ጠቀሜታ ያስረዳሉ።

በግብፅ በኩል የቀረበውን የዓለም ባንክ ተሳትፎን በተመለከተ የባንኩን የአዲስ አበባ ፅህፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጠን በጠየቅነው መሰረት በኢሜል ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል።

''ሦስቱ አገራት በጋራ የዓለም ባንክ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርግ በይፋ ከመጠየቃቸው በፊት የግብፅ ባለሥልጣናት ቀርበው በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያንና የሱዳንን ይሁንታ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልፀውልናል። የዓለም ባንክ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውስጥ ምንም ተሳትፎ የለውም'' የሚል ምላሽ ሰጥቷል።