የካቡል ወታደራዊ ትምህርት ቤት ጥቃት ተፈፀመበት

ቅዳሜ በተፈፀመው ጥቃት ከተጎዱት መካከል አንዱ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ቅዳሜ በተፈፀመው ጥቃት ከተጎዱት መካከል አንዱ

በአፋጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ ከባድ ተኩስና ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘገበ።

በማርሻል ፋሂሚ ብሔራዊ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ ሊነጋጋ ሲል እንደሆነ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ይህ ዛሬ ሰኞ ንጋት ላይ የተፈፀመውጥቃት ከቀናት በፊት ፈንጂ በጫነ አምቡላንስ ተፈጽሞ በትንሹ 100 ሰዎችን የገደለው ከባድ ጥቃት ካጋጠመ ከቀናት በኋላ ነው።

እስላማዊ መንግሥት የተባለውና የታሊባን ቡድኖች በቅርቡ የተለያዩ ጥቃቶችን በከተማዋ ውስጥ መፈፀማቸው ይታወሳል።

ንጋት 11 ሰዓት ላይ ጥቃቱ በተፈፀመበት ጊዜ በርካታ የፍንዳታዎች እና የቀላል መሳሪያ ተኩስ እንደተሰማ የቢቢሲው ማህፉዝ ዙቤይዳ ከካቡል ዘግቧል።

ቶሎ የተሰኘው የአፍጋኒስታን ዜና ተቋማ እንደዘገበው የፀጥታ ኃይሎች በጥቃቱ አካባቢ የሚገኙ መንገዶችን በሙሉ ዘግተዋል።

በተጨማሪም የፕሬዝዳንቱ ቃል-አቀባይ ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከማሰልጠኛው የመጀመሪያ በር አልፈው መግባት እንዳልቻሉ በመግለፅ ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠዋል።

ኤኤፍፒ ዜና ወኪል የፖሊስ ቃል-አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው ደግሞ የሮኬትና የቀላል ጦር መሳሪያ ተኩስ እንደነበረ ነገር ግን አሁን ሁሉም ነገር ሰላም እንደሆነ ዘግቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ በወታደራዊ ማሰልጠኛው ውስጥ ተኩስ እንደተሰማ ነገር ግን በታጣቂዎች የተፈፀመ ጥቃት ነው ብሎ ለማለት ጥርት ያለ መረጃ እንደሌለው ፖሊስ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግሯል።

ሌሎች ዘገባዎች በጥቃቱ የተወሰኑ ታጣቂዎች መገደላቸውን አመልክተዋል።

ቅዳሜ ዕለት ያጋጠመው የአምቡላንስ ጥቃት ከሳምንት በፊት ካቡል በሚገኝ አንድ ሆቴል ላይ ከተፈፀመውና አብዛኞቹ የውጪ ዜጎች የሆኑ 22 ሰዎች ከተገደሉበት ጥቃት በኋላ የተከሰተ ነው። ታሊባንም ሁለቱን ጥቃቶች መፈፀሙን አሳውቋል።

የአፍጋኒስታን መንግሥት ወታደራዊ ተቋማት በተደጋጋሚ የታጣቂዎች የትቃት ኢላማ ሲሆኑ ቆይተዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ዛሬ ጥቃት በተፈፀመበትና በመሃል ካቡል በሚገኘው ከማርሻል ፋሂሚ ወታደራዊ ትምህርት ቤት ውጪ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት 15 እጩ መኮንኖች ተገድለው ነበር።