የትራምፕ እና የጄይዚ እስጥአገባ

Donald Trump and Jay-Z Image copyright Getty Images

ታዋቂው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ጄይዚ ትራምፕ ለአፍሪካ-አሜሪካዊያን የሚያሳዩትን ንቀት አስመልክቶ "ትልቅ ደም መጣጭ" ሲል አስተያየቱን የሰጠ ሲሆን እሳቸውም በአፀፋው ምላሽ ሰጥተዋል።

በትዊተር ገፃቸውም "በታሪክ ውስጥ የጥቁሮችን የሥራ አጥነት ቁጥር ወደታች እንደወረደ የተመዘገበው በእኔ አስተዳደር ነው" ብለው አስፍረዋል።

የአፍሪካ-አሜሪካዊያን የሥራ አጥነትም ታይቶ በማይታወወቅ ሁኔታ ወደ 6.8 % አሽቆልቁሏል።

ነገር ግን በተቃራኒው ተችዎች እንደሚሉት የኢኮኖሚ እድገቱ የተጀመረው በኦባማ አስተዳደር ወቅት ሲሆን አሁንም ቢሆን የጥቁሮች ሥራ አጥ ቁጥር ከነጮች ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ መሆኑን ነው።

ጄይዚ በሲኤንኤን 'ዘቫን ጆንስ' በተባለው ፕሮግራም ላይ ቀርቦ እንደተናገረው የሥራ አጥነት ቁጥር ላይ ማተኮር "ነጥቡን መሳት ነው" ብሏል።

"ዋናው ነገር ገንዘብ አይደለም። ገንዘብ ከደስታ ጋር አይወዳደርም፤ ሊወዳደር አይችልም። ይህን ማድረግ አጠቃላይ ነጥቡን መሳት ነው። ሰዎች በሰብአዊነታቸው ሊታዩ ይገባል። በሰውነታቸው ሊከበሩ ይገባል፤ ዋናው ነጥብ እሱ ነው" ሲል ተናግሯል።

ቀጥሎም የትራምፕ ምርጫውን ማሸነፍ ችግሮችን በትክክለኛው መንገድ ያለመፍታት ያመጣው ውድቀት እንደሆነም ተናግሯል።

"በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ላይ ሽቶ መርጨት እንደማለት ነው" ያለው ጄይዚ ጨምሮም " ቆሻሻውን ከማስወገድ ይልቅ የሚረጨውን እየረጩ ተቀባይ እንዲሆን ማድረግ ነው። እነዚህ ነገሮች ሲያድጉ ትንሽ የነበረው እንስሳ ወደ ትልቅ ደም መጣጭ እንስሳነት ይቀየራል። እናም እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያለ ትልቅ የደም መጣጭ እንስሳ ተፈጠረ" ብሏል።

ጄይዚ የባራክ ኦባማን አስተዳደር ይደግፍ የነበረ ሲሆን ለሂላሪ ክሊንተንም ድጋፉን ሰጥቷል።

የአፍሪካ አገራትን አስመልክቶ "ቆሻሻ" ያሉበትን ፀያፍ ስድብንም አስመልክቶ ለተጠየቀውም ጥያቄ "በጣም የሚያሳዝንና የሚጎዳ ነው። ሁሉም ሰው ተናዷል። ከንዴቱም በተጨማሪ ይህንን ሁሉ ህዝብ በንቀት ማየቱ የሚጎዳ ነውም" ብሏል።

ትራምፕ በበኩላቸው "ዘረኛ" ናቸው የሚለውን ውንጀላ ነው በማለት የካዱ ሲሆን፤ የተጠቀሙበት ቃል ምንም እንኳን "ጠንከር" ያለ ቢሆንም የአዘጋገቡ ቃላት አጠቃቀም የተሳሳተ ነው በሚል አለመስማማታቸው ተዘግቧል።