ለናይጄሪያዊቷ ፀሃፊ ባቀረበችው ጥያቄ የተጋለጠቸው ጋዜጠኛ

Chimamanda Ngozi Adichie Image copyright AFP/Getty Images

ካሮላይን ሙህ የተባለች የፈረንሳይ ጋዜጠኛ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘችው ናይጄሪያዊቷ ፀሃፊ ችማማንዳ አዲቼን "ናይጄሪያ ውስጥ ቤተ መፃህፍት አሉ? መፅሃፎችሽስ ይነበባሉ?" ስትል መጠየቋን ተከትሎ 16 ሺህ ሰዎች ስለጉዳዩና ስለ ቺማማንዳ ትዊት አድርገዋል።

13 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ጉዳዮን በማስመልከት ችማማንዳ ፌስቡክ ገጿ ላይ ላሰፈረችው ፅሁፍ በተለያየ መንገድ ምላሽ ሲሰጡ ሦስት ሺህ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል።

ባለፈው ሃሙስ ፓሪስ ላይ በተደረገ የቀጥታ ስርጭት ቃለ-ምልልስ ነበር ቺማማንዳ ከጋዜጠኛዋ ጥያቄው የቀረበላት።

የቺማማንዳ መልስ "በጣም በሚያስገርም መልኩ ያነባሉ" የሚል ነበር። መፅሃፏ በናይጄሪያ ብቻም ሳይሆን በመላው አፍሪካ እንደሚነበብም ጨምራ ገልፃለች።

በምርጥ ፀሃፊነቷ ዓለም ለሚያውቃት፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ላገኘቸውና በአሜሪካና በአውሮፓ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ለተሰጣት ቺማማንዳ የዚህ አይነት ጥያቄ ማቅረብ የጋዜጠኛዋን ዝግጅት ከማድረግ ይልቅ ግምቷን ይዛ ወደ ቃለ መጠይቁ መግባቷን አጋልጧል።

ጋዜጠኛዋ ፈረንሳይ ውስጥ ስለ ናይጄሪያ የሚነገረው ሁሉ ስለ ቦኮ ሃራምና ብጥብጥ ብቻ እንደሆነ በመጥቀስ ጥያቄዋን መሰረት ለማስያዝም ጥራ ነበር።

ጋዜጠኛዋ ስለ ናይጄሪያ ሥነ-ፅሁፍና የንባብ ባህል ግምቷን መሰረት አድርጋ ያቀረበችው ጥያቄ የፈረንሳይ ህዝብን ገፅታ የሚያበላሽ እንደሆነ ቺማማንዳ ተናግራለች።

በጋዜጠኛዋ የተበሳጩ ናይጄሪያዊያን እውቅ ፀሃፊ ዎሌ ሾይንካ፣ ቺንዋ አቼቤንና ቤን ኦርኪን በመጥቀስ ስለ ናይጄሪያ የሥነ-ፅሁፍ ከፍታ ለማስታወስ ተገደዋል።

በዚህ ዘመን አንብቦ ከመዘጋጀት ይልቅ ግምቱንና የራሱን ውስን የዓለም አተያይ መሰረት አድርጎ የሚሰራ ጋዜጠኛ መኖር አሳዛኝ እንደሆነ አስተያየታቸውን የሰጡም በርካቶች ናቸው።

ከቺማማንዳ መፅሃፎች አሜሪካና እና ፐርፕል ሄቢስከስን መጥቀስ ይቻላል።

"ዊ ሹድ ኦል ቢ ፌሚኒስትስ" የሚለው የቴድ ኤክስ ንግግሯ ደግሞ ወደ መፀሃፍ ተቀይሮ ስዊድን ውስጥ ለ16 ዓመት ልጆች በሙሉ ተሰጥቷል።

የንግግሩን ሃሳብ ቢዮንሴም በአንድ ዘፈኗ አካታዋለች።

ተያያዥ ርዕሶች