ካለሁበት 20፡ አንዳንድ ቦታዎች ጀጎልን ያስታውሱኛል

ሚካኤል ባሕሩ Image copyright Michael Bahiru

ሚካኤል ባሕሩ እባላለሁ። ተወልጄ ያደግሁት ሐረር ከተማ ሲሆን፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት አዲስ አበባ ነው። አሁን ያለሁት ደግሞ ሆላንድ ውስጥ አምስተርዳም ከተማ ነው።

ወደ እዚህ ሃገር የመጣሁት መጀመሪያ ሀገር ቤት በህክምና ትምህርት ከተመረቅሁ በኋላ ነው። ትምህርቴን ለመቀጠል በነበረኝ ፍላጎት ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት አመልክቼ ነበር። በመጨረሻም አሁን ያለሁበት ከተማ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎኝ ሁለተኛ ዲግሪ ለመስራት ነው የመጣሁት።

አምስተርዳምን ኢትዮጵያ ውስጥ ከኖርኩባቸው ከተሞች የተለየ የሚያደርገው በቀዳሚነት ቅዝቃዜዋ ነው። በተጨማሪ ሆላንድ ሜዳማ ስለሆነች እንደ ኢትዮጵያ ተራራ የመመለከት እድልህ ጠባብ ነው። አምስተርዳም ውስጥ ከፎቆቹ ባሻገር የምታይ ተራራ የለም ዙሪያው በህንፃዎች የተከበበ ነው።

ወደ ሆላንድ ከመጠሁ በኋላ አዘውትሬ የምመገበውና የምወደው በሳልመን ዓሳ የተዘጋጀ መግብ ነው። ከቤት ውጪ ምግብ ቤት እየሄድኩ መመገብን ስለማልመርጥ ብዙ ጊዜ እራሴ እየሰራሁ ነው የምመገበው። ስለዚህም ከዓሳ የሚዘጋጀውን ምግብ እመርጠዋለሁ።

Image copyright Michael Bahiru

ከሃገሬ ከወጣሁ አጭር ጊዜ ቢሆንም ስለሃገር ቤት ሳስብ ዘወትር የሚናፍቀኝ የሀገሬ ሰው ነው። ከሀገር ውጪ የተለየ ባህል ካላቸው ሰዎች ጋር በቀላሉ ተዋህዶ መኖር አስቸጋሪ በመሆኑ የማውቃቸው ሰዎች ይናፍቃሉ።

በህይወቴ ውስጥ የማውቃቸው ሰዎች በሙሉ ያሉት ሃገር ቤት ነው። ስለዚህ ከቤተሰቤ ጀምሮ ሁሉም ሰዎች ዘወትር ይናፍቁኛል።

ከቤቴ በመስኮት በኩል ወደውጪ ስመለከት በተለይ ጠዋት የማየው በበጋ ጊዜ ሲሆን ከምሥራቅ የምትወጣውን ፀሃይ ነው። አምስተርዳም ውስጥ አብዛኛው ሰው ለጤናውም ሲል ብስክሌት ተጠቃሚ ነው።

በተለይ ጠዋት በጣም ብዙ ብስክሌቶች ተደርድረው ቆመው በመስኮቴ በኩል እመለከታለሁ። እናም ጠዋት ላይ ቡናዬን እየጠጣሁ በመስኮት የምትገባውን ፀሃይ እየሞቅኩ ውጪውን መመልከት ደስ ያሰኘኛል።

አምስተርዳም ብዙ ነገሮች አሏት፤ ግን ቢኖራት ወይም ቢጨመርላት የምለው ነገር ተራራ ነው። ከተማዋ ሜዳማ ስለሆነች ተራራ ለማየት ይቸግራል ስለዚህ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ሃገሪተወ ተራራ ቢኖራት የበለጠ የተሟላ ትሆናለች ብዬ አስባለሁ።

ወንዞችና የሚያምሩ መስኮች በከተማዋ ውስጥ አሉ። በብስክሌትም ሆነ በእግሬ ስጓዝ አንድ ከፍ ያለቦታ ቢኖራቸው ወደዚያ ሄጄ የከተማዋን ዙሪያ ገባ ብመለከት ደስ ይለኛል። እናም ይህ እድል ቢኖር ጥሩ ስሜትን ይሰጣል ብዬ ስለማስብ ከተማዋ ተራራ ቢኖራት እላለሁ።

አሁን ግን በምታምረው ከተማ ውስጥ ዞር ዞር ብዬ ስትመለከት የተወሰነ ነገር ብቻ ነው ማየት የምችለው። እናም ከዛፎች ወይም ከህንፃዎች ጀርባ ምን እንዳለ ለማየት ያስቸግራል። በተለይ በከተማዋ ውስጥ ስትቆይ የመታፈን አይነት ስሜትን ይፈጥራል።

ስለዚህ አምስተርዳም ውስጥ ከፍ ብለው የሚታዩ ተራሮች ቢኖሩ በጣም ደስ ይለኝ ነበር።

Image copyright Michael Bahiru

አንዳንድ የአምስተርዳም አካባቢዎች ከትውልድ ከተማዬ ከሐረር ጋር ይመሳሰሉብኛል። በተለይ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተቃራርበው የተሰሩ ቤቶችና በተጠረቡ ድንጋዮች የተገነቡ የውስጥ ለውስጥ የከተማዋ መንገዶች ትንሽም ቢሆን ጀጎልን ያስታውሱኛል።

በተለይ በመጣሁበት ወቅት ወደ እነዚህ አካባቢዎች ስሄድ ድንቅ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ውጪ አብዛኛው የከተማው ክፍል እኔ ከማውቃቸው የሃገራችን አካባቢዎች ጋር ብዙም የሚያመሳስል ነገር የለውም።

እስካሁን እንደተማሪ አምስተርዳም ውስጥ በቆየሁበት ጊዜ የጎላ አስቸጋሪ ነገር አልገጠመኝም። ነገር ግን ለሃገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ ስለነበርኩ ሰዎችን ለመቅረብና ተዋውቆ ማህበራዊ ግንኙነትን ለመመስረት መጀመሪያ ላይ ተቸግሬ ነበር።

ይህም ከሃገርና ከቤተሰብ ናፍቆት እንዲሁም ከትምህርቱ ጫና ጋር ተያይዞ ከብዶኝ ነበር። ለሁለት ወራት ያህልም በዚህ ምክንያት ተቸግሬ ነበር። ከዚህ ውጪ ግን ፈጣሪ ይመስገን አሁን ለምጄ ሁሉ ነገር ጥሩ እየተሄደልኝ ነው።

አሁን ባለሁበት ሁኔታ ድንገት ብድግ ብዬ ወደ አንድ ቦታ መሄድ ብችል የምመርጠው ቦታ ሐረርን ነው። ቀጥታ ወደ ሐረር በመሄድ ጀጎል ውስጥ በመሆን ጣፋጭ ፍራፍሬዎቿንና ምግቦቿን እየበላሁ እራሴን ባገኝ ደስ ይለኛል።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 21፡በእንግሊዝ ሰው ወደየግል ጉዳዩ ነው የሚሯሯጠው

ካለሁበት 22፡ የተወለድኩባት፣ የቤተሰብ ፍቅርና ህይወት ያሞቃት ቤቴ ትናፍቀኛለች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ