በሞባይል ኢንተርኔት መቋረጥ የተገደቡ እንቅስቃሴዎች

ethio-telecom

ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ትላልቅ ከተሞች የሞባይል ኢንተርኔት ከተቋረጠ ከአንድ ወር በላይ እንደሆነና በዚህ መቸገራቸውንም ብዙዎች ይገልፃሉ። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተለያዩ ከተሞች ኗሪዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት መጠቀም አለመቻላቸው በብዙ መልኩ ተፅእኖ አሳድሮባቸዋል። ተማሪዎች ተጨማሪ ንባብ ማድረግ፤ መረጃዎችን ማግኘትም አልቻሉም።

በስልካቸው ኢንተርኔት የግል ሥራቸውን የሚያሳልጡም መቸገራቸውን እንዲሁም በቀላሉ መገናኘት ባለመቻላቸውም ማህበራዊ ግንኙነታቸው እንደተጎዳ የገለፁም አሉ።

በሃዋሳ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የግል ባንክ ውስጥ ሰራተኛ የሆነችው ሊዲያ ሳሙኤል ሥራ ለመፈለግም ሆነ መረጃ ለማግኘት ከዚህ በፊት የተለያዩ ድረ-ገፆችን ትከታተል እንደነበር አሁን ግን የኢንተርኔት ሞባይል ዳታ ስለተቋረጠ ይህን ማድረግ አለመቻሏን ትናገራለች።

በተጨማሪም የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ትምህርቷ ላይም ተፅኖ አለው።"የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ ጥናት እያደረግኩ ነው። ለዚህ መረጃ ያስፈልገኛል። ይሁን እንጂ ከሥራ ወጥቼ ዋይፋይ ሳስስ ነው ጊዜዬን የማጠፋው" ትላለች ሊዲያ።

ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው ውጭ አገር ያሉት ሰዎችም በሞባይል ዳታ ኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት እንደቀድሞ መገናኘት አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ገላኔ ፉፋ የተባለች የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሚሉት ቤተሰቦቻቸው ካልደወሉላቸው በስተቀር መገናኘት አለመቻላቸውንም ያስረዳሉ።

"ዶርማችን ቁጭ ብለን በሞባይል ኢንተርኔት በምናገኘው መረጃ የቤት ሥራዎችን እንሰራ ነበር። ተጨማሪ እውቀት ለማግኘትም መረጃ እናገኝ ነበር" የምትለው ገላኔ አሁን ግን ኢንተርኔት ለማግኘት ወጥተው በምሽት ዋይ ፋይ ያለበት ለመሄድ እንደሚገደዱ ትናገራለች።

በመቀለ ኗሪ የሆነው አቶ ፍፁም ብርሃነ ደግሞ ከአንድ ወር በፊት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በመቀሌና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች የሞባይል ኢንተርኔትና ሲዲኤምኤ መጠቀም እንዳልተቻለ ይናገራል።

"ኢሜል የምላላከው በሞባይል ኢንተርኔት ነበር። አሁን ግን ብሮድባንድ ኢንተርኔት ወዳለበት መሄድ ግድ ብሎኛል። ይህ ደግሞ ያላግባብ ጊዜዬን እንዳባክን አድርጓል" ይላል ፍፁም።

አገራዊና ዓለምአቀፋዊ አዳዲስ መረጃዎችን ከፌስቡክና ከሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ማግኘት ስላልተቻለ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ከአዲስ አበባ ሰዎች እየነገሩት እንደሆነም አመልክቷል።

"ይህ አገልግሎት ለምን እንደተቋረጠ አናውቅም። እንደ ምገምተው ግን አገሪቱን የገጠማት ያለመረጋጋት እንዳይስፋፋ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ግን ኢንተርኔት መዝጋት መፍትሄ አይሆንም"ይላል አቶ ፍፁም።

በደሴ ከተማ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት ከተቋረጠ ሦስት ወር እንደሆነና በንግድ ሥራቸው ላይ ጉዳት እንዳስከተለ እንደዚሁም ከመንግሥት ሚዲያ ውጭ የተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገፅ መረጃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፀዋል።

ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልገው የጊንጪ ከተማ ነዋሪም መላ ቤተሰቡ አሜሪካ እንደሚገኝና ከእነሱ ጋር ያለው ግንኙነት ላለፉት ሁለት ወራት መቋረጡን ይናገራል።

"እናቴ፣ አባቴ፣ እህትና ወንድሞቼ አሜሪካ ነው የሚኖሩት። እኔ በምኖርበት ጊንጪ ደግሞ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት የተቋረጠው ከሁለት ወር በፊት ስለሆነ እንደ ድሮ ቤተሰቦቼን ማግኘት አልቻልኩም" ይላል።

እሱ እንደሚለው በቀጥታ መስመር ተደዋውሎ መገናኘት ከወጪው አንፃር የማይታሰብ ነው።

የአዳማው ነዋሪው ቤኛ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ላለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ኢንተርኔትን መዝጋት መፍትሄ እንደማይሆን ይናገራል።

"አዲስ አበባ ብቻ ነው ሞባይል ዳታ ኢንተርኔት የሚሰራው። እሱንም ከተፅኖ ለማምለጥ ይሆናል ያልዘጉት። ቀድሞውንም አገሪቱ የኢንተርኔት ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው። ይህ እርምጃ ደግሞ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። ይህ ውሳኔ ህዝቡንም አገሪቱንም ይጎዳታል" ይላል ቤኛ።

በተለያዩ ከተሞች የሞባይል ኢንተርኔት ከተቋረጠ አንድ ወር ሆኖታል መባሉን በተመለከተ የጠየቅናቸው የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደውሉልኝ ቢሉም ባሉት ሰዓት ስልካቸው ተዘግቷል። ከዚያ በኋላም ደጋግመን ብንሞክርም ስልካቸው ስለማይነሳ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በማህበራዊ ድረ ገፆች ለብዙዎች የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን የሚሰጡ፤ ለበጎ አላማ ሰዎችን የሚያስተባብሩ እንዲሁም የትምህርትና የሥራ እድልን የሚመለከቱ መረጃዎችን የሚያጋሩ ሰዎች እንቅስቃሴም በሞባይል ኢንተርኔት መዘጋት ተገድቧል።

አብዛኛውን ጊዜ መገናኛ ብዙሃን ምን ዘገቡ ብለው ቅኝታቸውን በስልክ የሚያደርጉ ሰዎች የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት መዘጋት ተፅእኖ ያሳድሮባቸዋል።

ከንግድ፣ ከጤና፣ ከፖለቲካና ከማህበራዊ ሁነቶች አንፃር ብዙዎች ከስልካቸውና ከኢንተርኔት ጋር ያለቸው ቁርኝት ከፍተኛ በሆነበት በዚህ ጊዜ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት ከአንድ ወርና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ መቋረጡ ተፅእኖው ከባድ እንደሆነ ቢቢሲ ያናገራቸው የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በመበደል ከዓለም ቀዳሚ ሃገራት አንዷ ነች ተባለ