ሳኡዲ ከ106 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከታሳሪዎች አስመለሰች

ቅንጡው የሪትዝ ካርልተን ሆቴል Image copyright Reuters

በቅርቡ ሳኡዲ አረቢያ ባካሄደችው የፀረ-ሙስና እርምጃ ሃገሪቱ 106.7 ቢሊዮን ዶላር ማስመለሷን የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቁ።

ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ ለጥያቄ ከተጠሩት 381 ሰዎች መካከል 56ቱ አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ሼክ ሳዑድ አል-ሞጄብ ገልፀዋል።

ታሳሪዎቹ የተለቀቁት ጥፋታቸውን አምነው የተለያዩ ንብረቶችን፣ ገንዘብና ሌሎች ሃብቶችን ለሳዑዲ መንግሥት ከሰጡ በኋላ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቤ-ሕጉ በዚህ ውስጥ ያለፉት እነማን እንደሆኑ ስማቸውን አልጠቀሱም። ነገር ግን የሃገሪቱ ልዑላን፣ ሚኒስትሮችና የንግድ ሰዎች እንደሚገኙበት ይነገራል።

ባለፈው ሳምንት ቢሊየነሩ ባለሃብት ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል እና የአረብ ሳተላይት ቴሌቪዥን የሆነው ኤምቢሲ ባለቤት አልዋሊድ አል-ኢብራሂም በሪያድ የዲፕሎማቶች ሰፈር ከሚገኘውና በእስር ከቆዩበት ቅንጡው የሪትዝ ካርልተን ሆቴል መለቀቃቸው ይታወሳል።

ሁለቱም ባለሃብቶች ንፁህ መሆናቸውን ቢናገሩም ለሳዑዲ ባለስልጣናት ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደሚሉት ''ጥፋት'' መፈፀማቸውን አምነው በገንዘብ ለመካስ መስማማታቸውን ይገልፃሉ።

የቀድሞው ንጉሥ አብዱላህ ልጅ የሆነውን ልዑል ሚቴብ ቢን አብዱላህን ጨምሮ የተለቀቁት ሰዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ንብረትን ለመንግሥት ካስረከቡ በኋላ ነው።

ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ኢብራሂም አል-አሳፋ ግን ምንም አይነት ጥፋት አለመፈፀማቸው ተረጋግጦ ነፃ እንደወጡ ተዘግቧል።

አቃቤ ሕጉ እንዳሉት አሁንም በእስር ላይ ከሚገኙት 56 ሰዎች ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ጉዳይ ተቀባይነት ያላገኘው ''ገና በሂደት ላይ ባሉ ሌሎች የወንጀል ክሶች ወይም ምርመራውን መቀጠል'' በማስፈለጉ እንደሆነ ገልፀዋል።

ታሳሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ከቅንጡው የሪትዝ ካርልተን ሆቴል ወደ ሌላ እስር ቤት መዘዋወራቸው የሚታመን ሲሆን ሆቴሉ በቀጣዩ ወር ለተገልጋዮች ክፍት ይሆናል ተብሏል።

የሳኡዲ ገንዘብ ሚኒስትር የሆኑት ሞሃመድ አል-ጃዳን ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ከታሳሪዎቹ በስምምነት የተመለሰው ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ዜጎች የኑሮ ውድነትን እንዲቋቋሙ ለሚያስችል ተግባር ይውላል ብለዋል።

ይህ የፀረ-ሙስና ዘመቻ የተጀመረው የንጉሥ ሳልማን ልጅ በሆነው በወጣቱ አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን ሲሆን አንዳንዶች ተቀናቃኞቹን ዞር ለመድረግ የተወሰደ እርምጃ ነው ይላሉ። ነገር ግን አልጋ ወራሹ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ወደ ስልጣን ሲወጣ ከታሰሩት ውስጥ አብዛኞቹ ታማኝነታቸው ገልፀውለት ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች