የሰብአዊ መብት አያያዝና የመብት ተቆርቋሪዎች ሁኔታ

የሪፖርቱ ሽፋን ገፅ Image copyright AHRE

መቀመጫውን በሰዊዘርላንድ ጄኔቭ ያደረገው ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች ለኢትዮጵያ የተሰኘው ተቋም በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የመብቶች አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አውጥቷል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ያለውን ጫና በመገምገም እንዳሰፈረው በተለይ ጨቋኝ ያላቸው ህጎች ከወጡ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝና ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እየጠበበ ስለመጣው የመንቀሳቀሻ ስፍራ ላይ ትኩረት ሰጥቷል።

ጨምሮም በርካታ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ለእስር፣ ለሰቆቃና ለእንልግት ሲዳረጉ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡት ደግሞ በሃገር ውስጥ የሚፈፀምባቸውን ጥቃት በመሸሽ በስደት በህይወት መቆየትን መርጠዋል ይላል ሪፖርቱ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢኮኖሚያዊ ልማት እርምጃዎችን ቢያሳይም ሰብአዊ መብትን በተመለከተ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተዳከሙ ነው ሲል አመልክቷል።

ሪፖርቱን በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትና የመደራጀት መብት ችግር ውስጥ ስለሆነ ዜጎች ምን እንደሚያስቡ ለማሳወቅ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ ገልፀው፤ በተለያዩ የሃገሪት ክፍሎች እየታዩ ያሉ ተቃውሞዎች የዚህ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።

ጨምረውም ''ይህን ሁሉ እንቅፋት አልፈው በሰአብአዊ መብት ላይ የሚናገሩ ዜጎች የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበራት በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተዳረጉ ስለሆነ የሚፈጸምባቸውን በደል ለማሳወቅና በአጠቃላይም ሃገሪቱ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ለማሳየት የተዘጋጀ ሪፖርት ነው'' ብለዋለ።

በቅርቡ መንግሥት እስረኞችን ለመፍታት የደረሰበትን ውሳኔ ''አበረታች ቢሆንም እስካሁን ከእስር የተለቀቁ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አላየንም። ስለዚህ የተወሰኑ ታዋቂ ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን መንግሥት ሌሎችም መብታቸውን በመጠየቃቸው ለእስር የተዳረጉትን ግለሰቦችን በሙሉ መፍታት ይጠበቅበታል'' ብለዋል።

ከአወዛጋቢው የ1997 ምርጫ በኋላ የወጡት ህጎች በከፍተኛ ደረጃ የጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቸንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን መንቀሳቀሻ ማሳጣቱን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሲቪል ማህበረሰቡ ለጋዜጠኞች ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አምደኞች እና ሃሳባቸውን በተለያየ መልኩ ለሚገልፁ ግለሰቦች አመቺ ሁኔታ የለም የሚሉት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይህ ደግሞ የሆነው መንግሥት ሁሉን ነገር እያዳፈነ በመምጣቱ ነው ይላሉ።

ሪፖርቱ ጨምሮም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀማቸው በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በሺዎች የሚቆጠሩት ለእስር ተዳርገዋል።

አቶ ያሬድም ''ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሰሜን ወሎ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ተቃውሞን ባሰሙ ሰዎች ላይ የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎች እጅግ አሳሳቢ እንደሆኑ'' ጠቅሰዋል።

የስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች ለኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ለመንግስትም ሆነ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ለማሻሻል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሪፖርቱ የመፍትሔ ሃሳቦችን እንዳስቀመጠ ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት ሪፖርቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አፋኝ ሆነውና በሕገ-መንግሥቱ ጭምር ጥበቃ የተደረገላቸውን የዜጎችን ነፃነት የሚገድቡ ሕጎችን በአጠቃላይ በአስቸኳይ እንዲቀየሩ የሚለውን ሃሳብ አንስቷል።

በተጨማሪም ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲከኞችና በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተይዘው የታሰሩ በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ሪፖርቱ ይጠይቃል።

ያለውን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት መንግሥት የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅን ልቦና ሃገራዊ መግባባትን የሚያመጣ ውይይት እንዲያደርግ ሃሳብ አቅርቧል።

በተለይ ደግሞ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ ጥይት በመተኮስ የሚወሰዱ እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ሪፖርቱ አፅንኦት መስጠቱን አቶ ያሬድ አመልክተዋል።