ደቡብ አፍሪካ፡መውጫ አጥተው የነበሩ 955 የማእድን ቁፋሮ ሰራተኞች ወጡ

The helmet and lamp of a miner (archive shot) Image copyright AFP

ወደ 955 የሚሆኑ ሰራተኞች በደቡብ አፍሪካ የማዕድን ማምረቻ ሰፍራ በአውሎ ንፋስ አማካኝነት መብራት በመጥፋቱ ከእሮብ ምሸት ጀምሮ መውጣት እንዳልቻሉ ተዘግቧል።

መብራት ከመቋረጡም ጋር ተያይዞ አሳንሰሮቹ ባለመስራታቸው በማታ ፈረቃ የሚሰሩትን ሰራተኞች ከመሬት ስር ማውጣት አልቻሉም።

የአሰሪው ኩባንያ ቃል አቀባይ በበኩሉ ሁሉም ደህና ናቸው ብሏል።

በተቃራኒው የሰራተኛ ማህበሩ ኃላፊዎች ከሮብ ምሽት ጀምሮ ከመሬት ስር ተቀርቅረው መቆየታቸው ለህይወታቸው ፈርተው እንደነበር ገልፀዋል።

ደቡብ አፍሪካ በአለም ላይ ካሉ ከፍተኛ ወርቅ አምራች አንዷ ስትሆን ነገር ግን ኢንዱስትሪው ሰራተኞችን ዝቅተኛ ደመወዝ በመክፈልና ሁኔታቸውም መጥፎ እንደሆነም ይነገራል።

ከጆሀንስበርግ በ290 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ቢትሪክስ የማእድን ቁፋሮ ስፍራ ባለቤትነቱም ሲባንየ ስቲል ዋተር የሚባል ኩባንያም ነው።

ወደ ላይ 23 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ከመሬት በታችም አንድ ሺ ሜትር ወደታች ጥልቀት አለው

"ሁሉም ሰራተኞች በደህና ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። ውሃና ምግብም እያቀረብንላቸው ነው" በማለት የኩባንያው ቃል አቀባይ ጄምስ ዌልስቴድ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

ኢንጅነሮቹም ጄነሬተሩን ማስነሳት ባለመቻላቻውም አሳንሰሮቹን ማስነሳት እንዳልቻሉ በተጨማሪ ተናግረዋል።

"ይህንን ችግር ለመቅረፍም ተግተን እየሰራን ነው" በማለት ጄምስ ዌልስቴድ ተናግረዋል።

አገር አቀፉ የማዕድን ሰራተኞች ማህበር በበኩሉ የአድን ስራ የተንቀራፈፈ ነው ሲሉ ተችተውታል።

"ዋናው ችግራቸው የተቀናጀ ባለመሆኑ በአንድ ጊዜ ማዳን የሚችሉት አንድ ሰራተኛ ነው። በጣም አስጨንቆናልም" በማለት የማህበሩ ቃል አቀባይ ሊቩህዋኒ ማምቡሩ ተናግረዋል።

የሰራተኞቹ ቁጥር ከፍተኛ ከመሆን ጋርም ተያይዞ የውሃ እጥረት እንዲሁም የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ማህበሩ ፍራቻ ነበረው።

"የማዕድን ቁፋሮ አደገኛ ስራ ነው። የእለት ምግባቸውን ለማግኘትና ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ሲሉም የማዕድን ቆፋሪዎችም ህይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ" በማለት የማህበሩ መሪ ጆሴፍ ማቱንጃዋ ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ አደገኛና ጥልቅ የሚባሉ የማዕድን ቁፋሮዎች የሚገኙባት ናት።

በባለፈው አውሮፓውያኑ አመት በአገሪቷ ውስጥ ከማእድን ቁፈሮም ጋር በተያያዘ ከ80 በላይ ሞቶችም ተመዝግበዋል

ተያያዥ ርዕሶች