አስጊነቱ እየጨመረ ያለው ካንሰር

በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የካንሰር ህሙማን ሴቶች ናቸው Image copyright LUIS ROBAYO

አቶ ወንዱ በቀለ የሁለት ዓመት ልጃቸውን በካንሰር ምክንያት በሞት ሲነጠቁ የህይወት መስመራቸው የተቀየረው እስከወዲያኛው ነው ።

ላለፉት አስራ አራት ዓመታት በልጃቸው ስም ባቋቋሙት "ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ"ለታማሚዎች እንክብክካቤ ማቀረብ እንዲሁም ስለበሽታው ግንዛቤ መፍጠርን የህይወታቸው ግብ ከማድረጋቸውም ባለፈ ተቋሙን ማስተዳደር አሁን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው ነው።

ማቴዎስ ያልተጠበቀና በእርጅና የመጣ ልጅ ቢሆንም አዲስ በረከትን ይዞላቸው እንደመጣ የሚናገሩት አቶ ወንዱ " የማቴዎስ መወለድ ህይወታችንን በጣም ነው የቀየረው" ይላሉ።

በሁለት ዓመቱ ህመም ሲሰማው ወደ ህክምና ይዘውት በሄዱበት ወቅት ነው የደም ካንሰር እንዳለበት የተነገራቸው።

ህክምናውም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጀመረ።

አቶ ወንዱ እንደሚናገሩት መድሃኒቶቹ ኃገር ውስጥም ስለሌሉ ከውጭ ነበር የሚያስመጡት።

ከሁለት ከሶስት ወር በኋላ ታክሞ ይድናል የሚል ተስፋን ቢሰንቁም እያገረሸበት መጣ እናም ከህክምና ማዕከሉም የተሰጣቸውም ምላሽ " ህክምናው እዚህ ሀገር የለም ውጭ አገር ይዛችሁት ሂዱ የሚል ነው" በማለት አቶ ወንዱ ይናገራሉ።

በኬሞ ቴራፒው ምክንያት ማቴዎስ ስለተዳከመ አውሮፕላን ላይ መውጣት እንዳልቻለ አቶ ወንዱ ይናገራሉ።

"ማቲ የተሻለ ህክምና ማግኘት እየቻለ ህክምናው ኢትዮጵያ ባለመኖሩ ብቻ አይናችን እያየ ከዚህ አለም በሞት ተለየ" ይላሉ።

ህክምናው በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ወንዱ በአፉም ደም ይተፋና ተስፋ አስቆራጭም እንደነበር ነው።

"ከዚህም የተነሳ ራሴን ለማጥፋት ያሰብኩበት ጊዜ ነበር" ይላሉ።

ከአስራ ዓመታት በኋላ የሀገሪቱን የካንሰር የጤና ሽፋን በሚመለከቱበት ጊዜ ለውጥ እንዳለ የሚመለከቱት አቶ ወንድ በመንግሥት ደረጃ የተቋቋመው የአገር አቀፍ የካንሰር መቆጣጠሪያ እቅድ ከሁለት አመት በፊት መውጣቱ እንዲሁም ጎንደር፣ መቀሌና ጅማ ትልልቅ የካንሰር የግንባታ ማእከል እየተሰራ መሆኑ ነው።

አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ወንዱ ከነዚህም ውስጥ መድሃኒቶች በበቂ አለመገኘት፣የባለሙያዎች ከፍተኛ እጥረትን ይጠቅሳሉ።

በተለይም ከህፃናት የካንሰር ህክምና ጋር ተያይዞ ሶስት የህክምና ባለሙያዎች ብቻ እንዳሉ ይናገራሉ።

አሁን በሚሰሩት ስራ ከፍተኛ እርካታ የሚሰማቸው አቶ ወንዱ "ሰው በረዳን ቁጥር ልጃችንን እንደረዳን ወይም ወደ ልጃችን እንደቀረብን ነው የምናስበው" ይላሉ።

Image copyright ANNE-CHRISTINE POUJOULAT

ካንሰር በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያካንሰር በርካቶችን በዋናነት ለህልፈት ከሚያበቁ ተላላፊ ያልሆኑ አራት በሽታዎች አንዱ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይገልፃል።

በኢትዮጵያ ምዝገባ ባለመኖሩ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ የሚያዳግት መሆኑን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ማቴዎስ አሰፋ ናቸው።

በአዲስ አበባ ውስጥ ባለ የካንሰር ምዝገባ ወደ 8500 አዳዲስ የካንሰር ህሙማን የሚመጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 2/3ኛው ሴቶች መሆናቸውን ዶ/ር ማቴዎስ ይናገራሉ።

ከዚህም የተነሳ የዓለም ጤና ድርጅት በየዓመቱ 60ሺ አዳዲስ የካንሰር ህመምተኞች እንደሚኖሩ መጠቆሙን ዶ/ር ማቴዎስ ጨምረው ያስረዳሉ።

በሴቶች ላይ 30% የሚሆነው የጡት ካንሰር አንደኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የአንጀት ካንሰር እንደሆነ ዶ/ር ማቴዎስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በወንዶች ላይ ደግሞ በአንደኛ ደረጃ የትልቁ አንጀት ካንሰር፣ በሁለተኛ ደረጃ የፕሮስቴት ካንሰር እና ከተለያዪ እጢዎች የሚነሱ የካንሰር አይነቶችን ይጠቀሳሉ።

ዶክተር ማቴዎስ ለካንሰር ከሚያጋልጡ ጉዳዮች መካከል ብለው የሚጠቅሷቸው የእድሜ መጨመር፣ ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ሁኔታ ይህም ብዙ ቅባት ያለው ምግብና ስጋን መመገብ፣ ትምባሆ ማጨስ፣ መጠን ያለው አልኮል መጠጣት እንዲሁም ኢንፌክሽንና ከቫይረስ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ምንም እንኳን በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የካንሰር ህሙማን ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ቢሆንም የህክምና አቅርቦቱ አመታት የሚጠበቅበትና ብዙዎች ያሰላቸ መሆኑም ይነገርለታል።

የካንሰር ህክምና ተደራሽነት

የህክምና ተደራሽነቱን በተለመለከተ ለዶክተር ማቴዎስ ቢቢሲ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር የትኛውም ሀገር ቢሆን የካንሰር ቁጥጥር ፕሮግራም ሊኖረው ይገባል የሚሉት ባለሙያው የመጀመሪያው ቀዳሚ ነገር መከላከል እንደሆነ ይናገራሉ።

" አልኮል መጠጥን መቀነስ፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ዋነኛው ነገር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከኢንፌክሽን ጋር የተያያዙ ካንሰሮችንም መቀነስ ይቻላል። ይህም አዋጭና ብዙ ዋጋ የማይጠይቅ ነገር ነው። "በማለት ባለሙያው ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ካንሰሩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሳያድግ ቅድመ-ካንሰር ምርመራ ማድረግ ይሄም ለጡትና ለማህፀን ጫፍ ካንሰር ሳይብስ በፍጥነት ህክምና ማድረግን እንደሚያስችል ዶክተር ማቴዎስ ይናገራሉ።

ከቅድመ-ምርመራ ጋርም በተያያዘ ክፍተቶች እንዳሉም ያስረዳሉ።

ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ህክምናው የተወሳሰበ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ማቴዎስ የቀዶ ጥገና፣ የጨረር፣ የሆርሞንና የኬሞ ቴራፒ ህክምና ደረጃ በደረጃ የሚሰጡና በዋጋም የማይቀመሱ መሆናቸውንም ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንድ የካንሰር የህክምና ማዕከል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን ሁለት የጨረር ህክምና መስጫ ብቻ መሆኑ የህክምናው ተደራሽነት ያለውን ክፍተት ማሳያ መሆኑን ዶክተር ማቴዎስ ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የባለሙያዎች እጥረት ሌላው ችግር እንደሆነ ይገልፃሉ።

ይህንንም ሁኔታ ለማሻሻል አንዳንድ ጅምሮች እንዳሉ የሚናገሩት ዶክተር ማቴዎስ ከነዚህም ውስጥ በተለያዩ ከተሞች በአዋሳ፣ በመቀሌ፣ በጅማ፣ በሀረማያ እንዲሁም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከላት እየተገነቡ መሆናቸው ነው።

የባለሙያዎችንም እጥረት ለመቅረፍ እንዲሁ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በካንሰር ህክምና ተማሪዎችንም እያሰለጠኑ ነው።

በተጓዳኝም የሜዲካል ፊዚክስ፣ የጨረር ህክምና ስፔሻሊስት ትምህርቱ በሀገር ውስጥ ያልነበረ ቢሆንም በቅርቡ እንደሚጀመርም ዶክተር ማቴዎስ ይናገራሉ።