"የኔ ጉዳይ የድርጅት ብቻ አይደለም" ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን በአዳማ ባደረገው ስብሰባ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶከተር ነጋሶ ጊዳዳየተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ ወስኗል።

ዶክተር ነጋሶ የኢትዮጵያ ፌዴራለዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የነበሩት በ1987 ዓ.ም ሲሆን ለሰባት ዓመታትም በስልጣን ቆይተዋል።

ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ለአራት ዓመታት ቀድሞ በፕሬዚዳንትነታቸው የሚገባቸውን ጥቅማጥቅሞች ቢያገኙም በግል ተወዳድረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላማ አባል ከሆኑ በኋላ ጥቅማ ጥቅሞቹ ተቋርጠዋል።

በአሁኑ ስብሰባም ላይ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ባይጠቅሱም ገንዘብ እንደተሰጣቸው ዶከተር ነጋሶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጣቸውና መኪናም እንደሚገዛላቸው ከኦህዴድ ቃል እንደተገባላቸው ተናግረዋል።

"ከ13 ዓመታት በኋላም ቢሆን ተሰምቷቸው ይሄንን ስለወሰኑ የኦህዴድ አመራር አመራርና በአጠቃላይ አባላቱን አመሰግናለሁ። ነገር ግን የኔ ጉዳይ የኔ ጉዳይ የድርጅት ብቻ አይደለም። " በማለት የሚናገሩት ዶክተር ነጋሶ

"እንደ ቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ያለኝ መብት ሊከበርልኝ ይገባል፤ ይህንንም ማድረግ ያለበት የፌዴራል መንግሥት ነው። " ብለዋል።

ዶክተር ነጋሶ ለዓመታትም ይተዳደሩበት የነበረው የጡረታ ደመወዝ በወር 2295 ነው።

"መጀመሪያ የተቀጣሁበት ህግ ተሻሽሏል ስለዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ጉዳየን እንደገና ሊያጤነው ይገባል። "ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች