የጣና ዕጣ ፈንታ ለገዳማቱ መነኮሳት አሳሳቢ ሆኗል

እማሆይ ወለተማርያም

በጣና ሐይቅ ላይ ያንዣዘብበውን አደጋ ለክፍላተ ዘመናት ያህል ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም ባህላዊ ቅርሶችን ጠብቀው ባቆዩት ገደማት እና አብያተ ክርስትያናት የሚያገለግሉ መነኮሳት እና መናንያን እንዳሳሰባቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።።

በሐይቁ ባሉ ደሴቶች ከአስራ አምስት ሺ ሕዝብ በላይ ይኖራሉ። ደሴቶቹ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስትያናት መቀመጫም ናቸው።

አባ ወልደሰንበት ያለፉትን ወደሃያ የሚጠጉ ዓመታት ያሳለፉት በጣና ሐይቅ ተከብባ የምትገኘውን የእንጦስ እየሱስ ገዳም በማገልገል ነው።

ከብዙሃን ተነጥለው ዕድሜያቸውም ለፀሎት ይስጡ እንጅ አካባቢውን ለሚያሳሳቡ ጉዳዮች ባይታወር ናቸው ማለት አይደለም።

ከሰሞኑ ጣናን ስለወረረው አረም የሚሰሙት ነገር ያሳሰባቸውም ለዚህ ነው።

"እምቦጭ አረሙ መጥቷል ማሽን እየተፈለገ ነው። አረሙ አስቸጋሪ እንደሆነም ሰማሁ። እኛማ ሃገር ከተቸገረ እኛም አብረን መቸገራችን ነው። ምን እናደርጋለን። እርሻ ላይ እንደገና ይበቅልበታል፤ እህልም ያበላሻል። ይህ ደግሞ ምን ዓይነት ፈተና ብዬ አዘንኩ። " በማለትም ይናገራሉ።

በጣና ሀይቅ ላይ ከሚገኙ የ37 የደሴት ገዳማት መካከል አንዱ የሆነው የክብራን እንጦንስ ኢየሱስ ገዳም መነኮሳትም ሀይቁ ላይ የተጋረጡት አደጋዎች አሳሳቢ ናቸው ይላሉ።

በቅርብ ርቀት ላይ ባለው የገዳሙ የሴቶች መኖሪያ ያገኘናቸው እማሆይ ወለተማርያም ስጋቱን ይጋራሉ። ችግሩን ለመመከትም ፀሎት መጀመራቸውንም ይናገራሉ።

"እምቦጭ አረም እዚህ አካባቢአይደለም ያለው። ጣና ቂርቆስ አካባቢ ነው። እኛ ሲነገር ነው የምንሰማው ቢሆንም በጣም ያሳቅቀናል" የሚሉት እማሆይ ወለተማርያም

"ጣና የእኛም ሆነ ሃገራችን ሃብት ነው። እኛ መሃል ላይ ስለሆንን ሊደርስብንም ላይደርስብንም ይችላል። ውሃውን እያመናመነ ሊያደርቀው ይችላልም ብለን እየተሳቀቅን ነው።

ስለዚህም እንጸልያለን። ጸሎት መናንያን የሚፀልዩት ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ዓለም ሁሉ ነው። እኔ ሳልሆን አባቶችና እናቶች ዘወትር የሚፀልዩት ለዓለም ነው። ዓለምን አድንልን ብለው ነው" ይላሉ።

ሆኖም የሐይቁን ደህንነት መጠበቅ የሰዎች ኃላፊነት መሆኑን መነኮሳቱ የሚያስረዱት አፅንኦት ሰጥተው ነው።

ለምሳሌ በአካባቢው ፋብሪካዎች እና ሆቴሎች የሚደርሰው ብክለት ለአባ ወልደሰንበት ሊታረም የሚገባው ጥፋት ነው።

"ኃጥያት ነው እንጅ ፤ በጣም እንጅ በሚገባ" ይላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች