ካለሁበት 21፡በእንግሊዝ ሰው ወደየግል ጉዳዩ ነው የሚሯሯጠው

ፍካረ ሃይለ Image copyright Fikare Hayle

ፍካረ ሃይለ እባላለሁ። በእንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ ነው የምኖረው። እዚህ ከተማ ውስጥ ለስምንት አመታት ቆይቻለሁ።

ታሪኬን ላውጋችሁ ከእኔጋ ቆዩ።

የተወለድኩት በአስመራ ከተማ ነው። በባህር ሃብት ሚኒስቴርም ተቀጥሬ እሰራ ነበር።

በወቅቱ አስመራ ላይ የነበረው አስተዳደር አሁን እንዳለው ዓይነት ኣልነበረም።

ለጥበብና ለስእል ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝ የስነ-ጥበብ ትምህርቴን ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ከ24 ዓመት በፊት መጣሁ።

ለሶስት ዓመታት ከተማርኩ በኋላም ትምህርቱን አቋርጨ ከአዲስአበባ ወደ ጣልያን የሚያስገባ ቪዛ ስላገኘሁ የተሻለ ትምህርት ለመከታተል በማሰብ ወደ ጣልያን አመራሁ።

ለ12 ዓመታትም ያህል በጣልያን አገር በህትመት ስራዎችና በማስዋብ (ዲኮሬሽን) ሰርቻለሁ።

ስደት እንዳሁኑ ፈታኝ አልነበረምና ብዙም ችግር አልገጠመኝም።

ከህንፃ አሰራር ጀምሮ ጣልያን ከኤርትራ ጋር የሚያመሳስሏት በርካታ ነገሮች ስላሉ የእንግድነት ስሜት አልተሰማኝም።

ራሴንም እንደ ስደተኛ አድርጌም አልቆጠርኩም። ጣልያን አሪፍ አገር ነች፤ተሰባስበንም አንድላይ ጥሩ ጊዜ እናሳልፍ ነበር።

ብዙ ሰዎች ኣንዴ ወደ ጣልያን ከገቡ መውጣት አይፈልጉም። እኔ ግን ለተሻለ ህይወት ኑሮየን ወደ ለንደን ቀየርኩኝ።

በእንግሊዝና በጣልያን አገራት የስደት ህይወት ተመሳሳይ አይደለም። በጣልያን አገር የማህበራዊ ቁርኝቱ ሰፊ ነው።

በእንግሊዝ ግን ሰው ወደ የግል ጉዳዩ ነው የሚሯሯጠው። ትዳር ራሱ በስደት በጣም ከባድ ነው።

የሰውን ልጅ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችን በማክበር ረገድ ግን በጣም የማደንቃት አገር ነች። በዚህ ረገድ ጣልያንና እንግሊዝ አይወዳደሩም ።

ጣልያን የስደተኞችን መብት በማክበር ብዙም ርቀት አልሄደችም። በእንግሊዝ ትምህርቴን ለመቀጠል ፍላጎት ቢኖረኝም ስራ ላይ ብቻ ነው ያተኮርኩት።

ሆኖም ስእልና ጥበቡን አልተውኩትም።

Image copyright Fikare Hayle

ስመራና ለንደን

ለንደን ከተማ ከአስመራ ጋር አይወዳደሩም። ለንደን በቴክኖሎጂ ረገድ በጣም ያደገች ከተማ ነች። ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው።

በተለይ ደግሞ በትራንስፖርት ዘርፍ ለንደን ላይ ያለው የትራንስፖርት ስርአት ከባቡር ጀምሮ እስከ አውቶብስ የተቀናጀ ነው።

በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚኖሩባት ለንደን ለሁሉም የሚበቃ ትራንስፖርት ማዘጋጀት ቀላል አይደለም።

በጣም ያስቀናል። ይሄስ የትራንስፖርት ስርዓት እኛ አገር ላይ በተዘረጋ ብዬ አስባለሁ።

ከምግብ ፓስታና ሽሮ እወዳለሁ ፤ ለማግኘትም አያስቸግርም።

Image copyright Fikare Hayle

ጥበብ እና ተፈጥሮ

ተፈጥሮ ለኔ ከፍተኛ የሆነ ደስታን ይሰጠኛል ፤ ለኔ ብዙ ትርጉም ስላለውም የምስላቸው ስእሎችም ከተፈጥሮ ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው።

የተፈጥሯዊ ውበት ባላቸው ቦታዎች ስሄድ በጣም እመሰጣለሁ።

በቦታው በመደመም አላበቃም ለህይወቴ መመርያ ሊሆነኝ የሚችል ብዙ ሃሳብ አመነጫለሁ።

ከለንደን መቀየር የምፈልገው ነገር ቢኖር በዚህ ከተማ የሚኖር ህዝባችን እንዲጠነክርና በአንድነት ተባብሮ ባየው ደስ ይለኛል።

ካገር ወጥቶ መኖር ቀላል አይደለም። በሰው አገር እየኖሩ አብሮህ ከሚኖሩ የአገርህ ልጆች ጋር በፍቅር እና በመተሳሰብ መኖር የማይቻልበት ሁኔታ አይኖርም።

በኤርትራ ያለንን ተስፋ የሚያጨልም ብዙ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ጊዜ የማይቀይረው ስለሌለ ሁሉም ነገር ሲሻሻል ወደ አገሬ የምመለስባት ቀን እናፍቃለሁ።

ስደት ላይ ላለ ሰው በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ላይ ሁሉም ነገር ከባድ ነው። ገንዘብ ቢኖር ራሱ ያስጨንቃል። እንግዳ በመሆናችን ሰው ራሱ ይሸሸነናል።

ረዥሙን ጊዜዬን የማሳልፈው በስራ በህትመት ስራዎችና በማስዋብ (ዲኮሬሽን) ነው። ንቅሳትን መንቀስ፣ የሞባይል እና የኤሌክትሮኒክስ ጥገና፣ ቅርፃ ቅርፅ እና ካፌ ውስጥ በትርፍ ግዜየ የምሰራባቸው ተጨማሪ ሙያዎቼ ናቸው።

የዚህ አገር የስደት ህይወት ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ለየት ያለ ነው። ችግር ብዙ ነገር ስለ ሚያስተምር የሚያጋጥሙንን ነገሮች በትእግስት ማለፍ አለብን።

በዚህ ሰአት ራሴን ወደ ሌላ ቦታ መላክ ብችል በርሬ ወደ አስመራ ከተማ በሄድኩ።

ለተመስገን ደበሳይ እንደነገረው።

ለኤደን ሃብተሚካኤል እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦

ካለሁበት 21፡በእንግሊዝ ሰው ወደየግል ጉዳዩ ነው የሚሯሯጠው

ካለሁበት 22፡ የተወለድኩባት፣ የቤተሰብ ፍቅርና ህይወት ያሞቃት ቤቴ ትናፍቀኛለች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ