አፍጋናዊቷ ስደተኛ በኢትዮጵያ

ከሪማ አብዱልሰጠር

ኑሯቸውን በቢሾፍቱ ከተማ ያደረጉትንና የአፍጋን ዜጋ የሆኑትን ከሪማ አብዱልሰጠር አማርኛን አቀላጥፈው ሲናገሩ ማየት መገረምን ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጡ 25 ዓመታትን ያስቆጠሩ ከአፍጋኒስታን የመጡ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንም በከተማ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኛም ብሎ መዝግቧቸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች በጦርነት ከሚተራመሱ አገራት እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ የሚመጡ ሲሆን ብዙዎችም በተለያዩ የስደተኛ መጠለያዎች ይቆያሉ።

በተለያየ ምክንያት መጠለያዎች ላይ መቆየት የማይችሉት በድርጅቱ እየተረዱም በከተማ ውስጥ መኖር የሚችሉ ተብለው አዲስ አበባ ውስጥ ይቆያሉ።

መጀመሪያ ኢትዮጵያ የመጡት በትዳር እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ከሪማ ሩሲያ በትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ለትምህርት የመጡት ኢትዮጵያዊ ባለቤታቸውንም እዛው ተዋወቁ።

ትንሽ ቆይተውም በሰርግ ተጋቡ "ድል ያለ ሰርግም ነበር" ይላሉ።

በወቅቱም አፍጋኒስታን መመለስ አስበው የነበረ ቢሆንም አፍጋኒስታን ኢትዮጵያዊ አግብተው ቢሄዱ ተቀባይነት እንደሌላቸውም ስላወቁ ባለቤታቸውንም ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

ሩሲያ በነበሩበት ወቅት ሁለት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ይዞ መምጣትም ስለከበዳቸው አፍጋኒስታን ለምትገኘው እህታቸው ሰጧት።

ልጆቻቸውን ወደ ኋላ ትቶ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በትዳራቸው ላይ ከፍተኛ እክልን ፈጠረ።

መጨቃጨቃቸውና ችግሮቻቸውም ተደራርበው በመጨረሻም ከአምስት ዓመታት የትዳር ቆይታ በኋላ እንደተለያዩ ወይዘሮ ከሪማ ይናገራሉ።

"አልፈልግሽም ውጪ አለኝ" የሚሉት ወይዘሮ ከሪማ አፍጋኒስታን በጦርነት የምትተራመስ ሀገር በመሆኗ ሊመለሱ አልቻሉም ከባለቤታቸውም ጋርም በመለያየታቸው የመኖሪያ ፈቃድ አልነበራቸውም ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ስደተኝነት ነበር።

አንድ የሚያውቁትም ሰው አማክሯቸው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንም ሄደው ተመዘገቡ፤ በጥቂት ወራትም ውስጥ የስደተኝነት ወረቀታቸውን አገኙ።

ብቸኝነቱም ሲብስባቸው ሶስት ኢትዮጵያውያን ልጆች በጉዲፈቻ እንደወስዱም ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የአፍጋን ዜጋ የለም፤ ችግርሽን የሚካፈል የሀገር ሰው የለም።" ይላሉ ወይዘሮ ከሪማ

ምንም አንኳን በቅርቡ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ባይችሉም ከጥቂት አመታት በፊት በኢራን ኤምባሲ አማካኝነት የት እንዳሉ የጠፉባቸውንም ቤተሰቦቻቸውን ስላገኙ ትንሽ እረፍት ፈጥሮላቸዋል።

ከልጆቻቸው ማሳደግ በተጨማሪም የምንጣፍ ስራዎችን፣ ልብስ ስፌትም ይሰሩ ነበር። "ገንዘብ የለም፤ ብቸኝነቱም ከባድ ነው። ስለዚህ ልጆቹንም ለማሳደግ ቀን ከሌት ነበር የምሰራው" ይላሉ።

ለሚያውቁዋቸው ሰዎች እንዲሁም የስደተኞች በዓል በሚኖርበት ወቅትም የእጅ ስራዎቻቸውን ይሸጣሉ።

ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት በየወሩ ሁለት ሺ ብር የሚሰጣቸው ሲሆን ይህም ብር በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ። " ሁለት ሺ ብር በአሁኑ ወቅት ሃያ ብር ማለት ነው" ይላሉ።

ወደ ሌላ ሀገርም ለመሄድ ጥረት ያደረጉ ሲሆን አሜሪካና ካናዳ ለመሄድ ሙከራ ባደረጉበት ወቅትም ለሁለተኛ ጊዜ ጉዳያቸው እንዲታይ ስለተመራም ተሰላችተው እንደተውት ይገልፃሉ።

"ከስደተኝነት ወጥቼ የኢትዮጵያ መኖሪያ ፍቃድ ባገኝ ደስ ይለኛልም" ይላሉ።

የወለዱዋቸው ወንዱ ልጃቸው ቤልጂየም በትምህርት ላይ ሲሆን ሴት ልጃቸው ነዋሪነቷ ቱርክ ነው።

ከሴት ልጃቸው ጋር በስልክ እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች የሚገናኙ ሲሆን ወንዱ ልጃቸው ጋር ግን ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም።

"ሴቷ ልጀ ትወደኛለች ወንዱ አይወደኝም። እንደ ባዳ ነው የሚያኝ፤ እዛው በቃ ባለችበት ትኑር ይላል" በማለት በሀዘኔታ ይናገራሉ።

ስለ ልጃቸው ብቻ ሳይሆን ስለ እህታቸው ሲያወሩ ለቅሶ የሚቀድማቸው ወይዘሮ ከሪማ "ሰው ቢያየን መንታ ነው የምንመስለው" ይላሉ።

ከሁለት ዓመታት በፊትም ልትጠይቃቸውም የመጣች ሲሆን ከሷም በተጨማሪ ከእህታቸውም ልጆች ጋር በስልክ እንደሚገናኙ ይናገራሉ።

ጦርነቱ ብዙ አሳጥቶኛል የሚሉት ወይዘሮ ከሪማ ከስምንት ወንድሞቻቸው ውስጥ አምስቱም በታሊባን ተገድለዋል ይላሉ።

አፍጋኒስታን ለመሄድም የተባበሩት መንግስታት ቢያመለክቱም ሀገሪቱ ሰላም ባለመሆኗ ቤተሰቦቻቸው እንዳይመጡም ከልክለዋቸዋል።

ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ወይዘሮ ከሪማ "ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤቴ ናት ፤ እናቴ ናት። ህዝቡ እንግዳ ይወዳል።" ይላሉ።

በማህበራዊ ኑሯቸውም የሚታወቁ ሲሆን እድር አላቸው፤ እቁብ ይጥላሉ። "የኢትዮጵያ ማህበራዊ ኑሮ ደስ ይላል፤ ለቅሶም ሲኖር ሰርግ አብረን እንሄዳለን። ልጅም ሲወልዱ ሄደን እንጠይቃለን። ገንፎ ባልወድም ያው እጠይቃለሁ" በማለት በሳቅ ይገልፁታል።

በዓላትም ሲሆን ከቻሉ ወደ መስጊድ ይሄዳሉ ፤ የአፍጋኒስታንም ምግብ ያበስላሉ።

ስለ አፍጋኒስታን ምግብም በዝርዝር ሲያወሩ አይጠግቡም። በተለይም ማንቱ ስለሚባለው ምግብ በዝርዝር ያወራሉ። በመጡበት ወቅት እንጀራ መብላት ከብዷቸው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ያው ባይመርጡትም እንጀራም ይመገባሉ።

በአሁኑ ወቅት በኩላሊት ህመም እየተሰቃዩ ሲሆን ኢትዮጵያውን ጎረቤቶቻቸው እያስታመሙዋቸው ነው። በሀያት ሆስፒታልም የዲያሊሲስ ህክምና የሚያደርጉ ሲሆን በሳምንት 3600 ብር ኮሚሽኑ ለህክምናው ሽፋን ያደርግላቸዋል።

"ምንም አልጎደለብኝም ጎረቤቶቼ ያስታምሙኛል። ከጎኔ ናቸው የመጀመሪያ ዘመዶቼ ጎረቤቶቼ ናቸው። በችግር ጊዜ ደራሸ እነሱ ናቸው። ግን ሁልጊዜም እህቴ ብትኖር፣ ወንድሜ ቢኖር እላለሁ። በጣም ይሰማኛል ከባድ ነው። ሀገር ሰላም ቢሆን እሄዳለሁ ሰላም የለም" በማለት በሳግ በተቆራረጠ ትንፋሻቸው እያለቀሱ ይናገራሉ።

ከጎረቤቷቸው መካከል ከሶሪያ የመጡ ስደተኞችም ሲኖሩ ጥብቅ ግንኙነትም አላቸው።

በአረብኛ ቋንቋም መነጋገራቸውም አገራቸውን አፍጋኒስታንንም ስለሚያስታውሳቸው በጣም ደስተኛ እንደሆኑ ይገልፃሉ። ምንም እንኳን አፍጋኒስታንን ቢናፍቁም ሶስት ልጆቻውን ትቶ የመሄድ እቅድ የላቸውም።

የመጨረሻ ልጃቸውን ተጥላ ሲሆን ያገኙዋት በአሁኑ ወቅትም የ17 ዓመት ዕድሜ አላት።

"ልጅ ማሳደግ በጣም ከባድ ነው። ጭንቀቱ ራሱ ይገላል" ይላሉ። "ወደ አፍጋኒስታን ተመልሸ አልሄድም። ነገር ግን እግዚአብሄር እድሜ ቢሰጠኝ ልጆቼን መዳር እፈልጋለሁም እንዲሁም ልጄን ለማየት ቱርክ ብሄድ ደስ ይለኛል" ይላሉ።