የቦረናን የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች አቆጣጠሮች ምን ይለየዋል?

Obbo Jaatanii Diidaa kaaraalandara Boranaa qabatanii

የቦረና የዘመን አቆጣጠር ከኦሮሞ ህዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ወይም የገዳ ሥርዓት መሰረት ነው።

የባህልና የታሪክ አጥኚ የሆኑት ጃተኒ ዲዳ የዘመን አቆጣጠሩ ቀንና ወራትን ከመቁጠር ባለፈ የዓለምን አፈጣጠር ቅደም ተከተል በውስጡ ያካተተ እንደሆነም ይናገራሉ።

ከዋክብትንም ስለሚያጠና ከሥነ-ፈለግ ጋር ከፍተኛ ትስስር አለው።

የዘመን አቆጣጠሩ እንደ ሌሎቹ አቆጣጠሮች ሃይማኖትን ሳይሆን ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ነው።

ሥለ ዘመን አቆጣጠሩ ማወቅ ያለባችሁ 11 ነጥቦች

 • የቦረና የዘመን አቆጣጠር 27 ቀናት አለው። እነዚህ ቀናትም አያና ይባላሉ። መጀመሪያም የተፈጠሩት አያና ሲሆኑ ከዚያም ጨረቃ ተፈጠረች። ይህ የዘመን አቆጣጠርም በአያናና በጨረቃ ላይ የተወሰነ ነው።
 • ድርጊቶች የተከናወኑባቸው ቀናት ከአመት አመት አይለያይም። ለምሳሌ አንድ ሰው ሰኞ ቢወለድ በዓመቱም ልደቱ በዛኑ ቀን ሰኞ ነው የሚከበረው። ቀኑን ሳይሆን ድርጊቱ የተፈፀመበት አያና ስለሚወስነው ነው።
 • አንድ ዓመቱ በ12 ወራት የተከፋፈለ ሲሆን እነዚህም አብራሳ፣አመጂ፣ጉራንደላ፣ቢቶቴሳ፣ጫምሳ፣ቡፋ፣ወጨበጂ፣ኦቦራጉዳ፣ ኦቦራጢቃ፣ብራ፣ጪቃ እና ሰደሳ ይባላሉ።
 • በዚህ ዘመንም አቆጣጠር ከአያናና ከጨረቃ ቀጥሎ የተፈጠረችው መሬት ናት። ይህም አብራሳ ተብሎ በሚታወቀው ወር ነው።
 • ከፍተኛ ሙቀት ያለው በአመጂ ወር ነው።
 • አስራ ሁለቱ ወራት አራቱ 31 ቀን ሲኖራቸው የተቀሩት ስምንት ወራት ደግሞ 30 ቀናት አላቸው።
 • ጫምሳ የሚባለው ወር ሁለት አያናዎች አሉት። ሶርሳ የሚባለው ፈረስ የተፈጠረበት አያና ሲሆን በዚሁ ቀንም መሬት የተንቀጠቀጠበትና ፈጣሪም መሬት ድንጋይ ላይ በማፍሰስ የተከላከለበት ቀን ነው። "የፈረስ ጉልበት" የሚለውም ቃል የመጣው ከፈረስ መፈጠርና ከመሬት መንቀጥቀጥ መቆምም ጋር ተያይዞ እንደመጣ ይታመናል።
 • መሬት በዚህ ቀንም የተንቀጠቀጠው የሰው ልጅ ኃጥያት ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱም ነው የሚል ዕምነት አለ።
 • ወጨበጂ የሚባለውም ወር ሰው ወደ ፈጣሪ የቀረበበት የዕርቅ ወር ተብሎ ይጠራል። ፈጣሪ ሰውንም ተፈጥሮንም የመረቀበትም ስለሆነ የገዳ ባህልም አመጣጥ ከዚህ ጊዜ ጋር ቁርኝት አለው ከዚህም ጋር ተያይዞ የገዳ ጉባኤ በዚሁ አያና ይደረጋል።
 • ብራ ፈጣሪ በሰው ልጅ ላይ ተቆጥቶ እያለ ሰውን የሚጎዱ እንስሳትም ሆነ ዕፅዋት የተፈጠሩበት ወር ነው ተብሎ ይታመናል።
 • 12ኛውና የመጨረሻው ወር ሳደሳ ቡናና በግ የተፈጠሩበት ቀን ነው። ቡናና በግ በባህሉ የዕርቅ ምልክቶች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ዕርቅ የሚካሄድበት ጊዜም በዚህ ወቅት ነው።

ይህ የዘመን አቆጣጠር የገዳ ስርዓት እስካሁን የሚተገበርባቸው አካባቢዎች እንደ ቦረናና ጉጂ ያሉ አካባቢዎች ይጠቀሙበታል።

ተያያዥ ርዕሶች