የግዕዝን ቋንቋ ለዘፈን?

ፀሐዬ ክንፈ Image copyright ፀሐዬ ክንፈ

ግእዝ በዓለማችን ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩት ቋንቋዎች አንዱ ነው።

በሃገራችን ለሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎችም መሰረት እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የቋንቋው ተናጋሪዎች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ በቤተ ክርስትያን ብቻ የተገደበ ሆኗል።

ይህንን ጥንታዊ ቋንቋ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም በጥንት ዘመን የተፃፉ መፃሕፍትንም ለመረዳት ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች በአሁኑ ወቅት እየቀነሰ መጥቷል።

እንደ ፀሐዬ ክንፈ ያሉት ግን የግእዝ ቋንቋን በተለየ መንገድ በማቅረብ በዘፈንም ይዞ የቀረበ ድምፃዊ ነው።

የግዕዝንም ቋንቋ ለዘፈንነት መጠቀም ሲጅምር ካደነቀውና ካበረታታው ይልቅ የሰደበውና ያጥላላው ሰው ይበዛ እንደነበር ይገልፃል።

በርግጥ ቁጥራችው ብዙ ባይባልም የተለያዩ ዘፈኖች ሲሰሩ በመግቢያ፣ በመሃል አለያም በመዝጊያ ላይ አንዳነድ የግዕዝ ቃላትን መጨመር አሁን አሁን እየተለመደ ነው።

ሙሉ ነጠላ ዜማ ከዛም አልፎ በአልበም ውስጥ በርከት ያሉ ዘፈኖችን ሰርቶ ለአድማጮች ማድረስ ግን ያልተለመደ ነው።

በቤተ ክርስተያን ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት እየተከታተለ ያደገው ድምፃዊ ፀሐዬ ግእዝ ቋንቋን ያጠናው በህፃንነቱ ነው።

ከዚያም ሙዚቃውን እንዴት በግዕዝ ቋንቋ ማድረግ እንደሚችልም ማሰብና ማሰላሰልም ጀመረ።

የመጀመርያውን ነጠላ ዜማ በግዕዝ ቋንቋም ሲስራም ምላሹ ጥሩ እንዳልነበር የሚናገረው ፀሐዬ ስድብና ርግማንም አጋጥሞኛል ይላል።

"የዚህም ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱን ቋንቋ እንዴት ታረክሳለህ" የሚል እንደነበረ ያስረዳል።

ቤተ-ክርሥቲያን ለግዕዝ ያላትን አስተዋፅኦ የሚያደንቀው ፀሐዬ ምንም እንኳን ድጋፍ የሚሰጠው ሰው ባይኖርም ተስፋ ሳይቆርጥ እንደገፋበትም ይናገራል።

" በርታ የሚሉኝ ጥቂቶች ነበሩ ቢሆኑም በዚህ ተስፋ አልቆረጥኩም አልበም ወደ ማዘጋጀቱ ቀጠልኩበት። ያን በመጥፋት ላይ ያለውን ቋንቋ በሙዚቃ ለማስቀጠልም ከተቻለ ወደ ነበረበት ለመመለስ ነው ዓላማዬ" ይላል ፀሐዬ።

ዜና ዜማ የሚል ስያሜ የሰጠውም ይህ አዲስ አልበምም 10 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን አራቱ በግእዝ የተሰሩ ናቸው።

ግጥሞቹን የሚያዘጋጀው ራሱ ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን አሳምረው የሚያውቁ ሰዎችንም በማናገር ነው።

ግጥሞቹ በሀገር፣ በማህበራዊ ህይወትና በፍቅር ላይ ያተኮሩ ሲሆን ከመጀመርያ ስራው በተሻለ ተቀባይነት እንዳገኙም ይናገራል።

"አብዛኛው ሰው ግእዝ የማይሰማና የማይናገር በመሆኑ ዘፈኖቹ ላይ የተወሰነ የትግርኛ ትርጉም ስለምሰራለት ምን እያልኩ እንደሆነ ይገባዋል።" በማለት ይገልፃል።

ግዕዝ ቋንቋን ለዘፈንነት በመጠቀሙ አዋረድከው በማለት የሰደቡትና የረገሙት ሰዎችም ከዚህ አልበም በኋላም ብርታትን እየለገሱት እንደሆነም ያስረዳል።

ፀሐዬ እስካሁን የሰራው ስራ እንደጅማሮ እንጂ እንደ ሙሉ ስራ እንደማይቆጥረውም ይናገራል።

ገና ወደ ስቱዲዮ ያልገቡ ስራዎች እንዳሉት የሚናገሩት ፀሐዬ የግዕዝን ታሪክን ለመጠበቅ ጥረት እንደሚያደርግም ይናገራል።

በተለይም ጥንታዊውን ቋንቋ ወደ ወጣቱ ትውልድ ለማስረፅ በባህላዊ መንገድ ከሚሰራው ዘፈን በተጨማሪ በዘመናዊ ሙዚቃ የግእዝ ዘፈኖችን የማዘጋጀት እቅድ አለው።

ተያያዥ ርዕሶች