እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌ በይቅርታ ሊፈቱ ነው ተባለ

እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌ Image copyright Facebook

ታዋቂው ጋዜጠኛ እና አምደኛ እስክንድር ነጋና የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌ በይቅርታ እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው ወደሦስት መቶ የሚጠጉ የፌዴራል ታራሚዎች መካከል እንደሚገኙ ለመንግስት የሚቀርብ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጠቅላይ አቃቤ ሕግን ጠቅሶ ዘግቧል።

አቶ እንዷለም ከአንድነት ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ መስራቾች መካከል አንደኛው ሲሆኑ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም ከታሰሩ በኋላ ለሽብር ጋር በተያያዘ በተመሰረተባቸው ክስ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወቃል።

እስክንድር በእስር ላይ ሳለ እ.ኤ.አ የ2012ን የፔን/ባርባራ ጎልድስሚዝ የፅሁፍ ነፃነት እና እ.ኤ.አ የ2017 የዓለም አቀፍ የፕሬስ ተቋምን የዓለም የፕሬስ ነፃነት የጀግንነት ሽልማትን ተቀዳጅቷል።

ሁለቱም የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች የሚያስተባብሉ ሲሆን የተለያዩ የዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች እስራታቸውን በፖለቲካ የተነሳሳ ነው በማለት ሲያጣጥሉት ቆይተዋል።

የፋና ዘገባ እንደሚለው ከሆነ ከፌዴራል እስር ቤቶች በይቅርታ ከሚወጡ ታራሚዎች በተጨማሪ ከአማራ ክልል እሴ ቤቶች ለሚገኙ 119 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።

ዘገባው ጨምሮ ታሳሪዎቹ የሚፈቱት በይቅርታ ቦርድ ለፕሬዚዳንቱ ከቀረበ፣ የተሃድሶ ስልጠናም ከወሰደ በኋላ ብሏል።

የጥፋተኝነት ፍርድ ከተላለፈባቸው እና የእስር ቅጣታቸውን በመፈፀም ላይ ከሚገኙት ውጭ ክሳቸው በመታየት ላይ ያለ 329 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ይደረጋልም ተብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ