በኢትዮጵያ የአዕምሮ ህሙማን ሰብዓዊ መብት እየተጣሰ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ውስጥ የአእምሮ ህመምተኝነት በባህሉም ሆነ በእምነት ከሰይጣን ወይም መጥፎ መናፍስት ጋር የተቆራኘ ነው ተብሎ ይታመናል።
በተለይም ከበድ ያለ የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ብዙዎችም መደብደብ፣ መንገላታት፣ መታሰር እንዲሁም በአጠቃላይ ከማህበረሰቡ መገለል ይደርስባቸዋል።
ብዙዎች ሲታመሙም ሃይማኖታዊ ፈውሶችን እንደ ፀበል፣ ፀሎት እንዲሁም ማህበረሰቡ አዋቂ ብሎ የሚፈርጃቸው ጋር ይሄዳሉ።
ወደ አዕምሮ የህክምና ማእከላት የሚመጡትም በነዚህ ቦታዎች ፈውስ ካላገኙ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይካትሪ ትምህርት ዘርፍ ክፍል አሶሺየት ፕሮፌሰር እንዲሁም አማኑኤል ሆስፒታል ለ12 ዓመታት ሀኪም ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ዮናስ ባህረ-ጥበብ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ከ360 በላይ የአዕምሮ ህመም እንዳለ የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ ማህበረሰቡ የአዕምሮ ህመም ብሎ የሚጠራው በራሳቸው ወይም በሰዎች ላይ ጠንቅ ማድረስ ሲጀምሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ህመማቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሰዎችም ማህበረሰቡ ራሳቸውም ላይ ሆነ ሌላው ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸውም በሚል ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ።
ይሄም የሚሆነው ለአዕምሮ ህሙማኑ ኃላፊነት የሚወስዱ ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት አካላት ስለሌሉ እንደሆነ ዶክተር ዮናስ ይናገራሉ።
"በነዚህ ሂደቶች የአዕምሮ ህሙማኑ ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፣ የሚታሰሩበት የእግር ሰንሰለት ከርክሯቸው ኢንፌክሽን ሊፈጥር ይችላል። መደብደብም ይኖራል" ይላሉ።
ይህ በማህበረሰቡ ያለው የአዕምሮ ህሙማን አያያዝም በአዕምሮ ህሙማን ማዕከላትም እየተደገመ እንደሆነ የህግ ባለሙያው አይተነው ደበበ "ቢሀይንድ ክሎዝድ ዶርስ ዘ ሂውማን ራይት ኮንዲሽንስ ኦፍ ፐርሰንስ ዊዝ ሜንታል ዲስኤብሊቲ ኢን ኢትዮጵያን ሳይካትሪክ ፋሲሊቲስ" በሚለው የድህረ ምረቃ መመረቂያ ፅሁፉ ውስጥ ይጠቅሳል።
የአእምሮ ህሙማን ምንም አይነት የህግ ከለላ የላቸውም የሚለው አቶ አይተነው የጤና ማእከላት ውስጥ የሚገቡት ጥቂቶቹ የአዕምሮ ህሙማን ታስረው እንዲሁም የህክምና አሰጣጡም ሰብአዊ መብትን የሚጥስ ነው ይላል።
ጥናቱ አማኑኤል ሆስፒታልና የገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከልንም አካቷል።
አከራካሪው ኤሌክትሮ ኮንቨልሲቭ ቴራፒ
ምንም እንኳን አንዳንድ የአዕምሮ ህሙማን ራሳቸውን የሚያውቁ እንዳሉ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን የማያውቁ የአዕምሮ ህመምተኞች አሉ።
እነዚህ ህሙማን መድሀኒት፣ምግብም ሆነ መጠጥ የማይወስዱበት ደረጃ ላይ በሚደርሱበት ወቅት በጤና ማዕከላት ውስጥ ከማደንዘዣ ጋር የኤሌክትሪክ ሾክ ይሰጣቸዋል።
የኤሌክትሪክ ሾኩ ከተሰጣቸው በኋላ እንደሚነቁም ምግብ ሊመገቡ እንደሚችሉ አይተነው ይናገራል።
ማደንዘዣ ተጨምሮ ኤሌክትሪክ ሾክ በሚሰጥበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ኤሌክትሪክ ስለሚተላለፍ ዘላቂ የሆነ የማስታወስ ችግር እንደሚገጥማቸው አቶ አይተነው ይናገራል።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶችን የሚጠቅሰው አይተነው "1/3 የሚሆኑት በኤሌክትሪካል ኮንቨልሲቭ ቴራፒ የታከሙ ሰዎች ዘላቂ የሆነ የመርሳት ችግር እንዲሁም የጭንቅላት ጉዳት ደርሶባቸዋል" ይላል።
በተቃራኒው ዶክተር ዮናስ "ኤሌክትሮ ኮንቨልሲቭ ቴራፒ ህይወትን ሊታደግ የሚችል ህክምና ነው፤ ያለሱ መስራት በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ነው፤ ምክንያቱም ህመምተኛው ለወራት አልበላም አልጠጣም ይላል፤ ካልጋም ላይወርድ ይችላል፤ የሰውነት አቅም እየደከመ ደሙም እየወረደ ይመጣል። ሊሞትም ይችላል" ይላሉ።
ዶክተር ዮናስ እንደሚናገሩት የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ይህ ህክምና ስለ አዳኝነቱ ብዙ እንደተባለለት ነው "ሁለት ወይም ሶስት ቴራፒ ሲሰጠው ህመምተኛው መብላት እንዲሁም መናገር ይጀምራል" ይላሉ።
ይህ ቴራፒ ከማደንዘዣ ጋር እንደሚሰጥ የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ ያለማደንዘዣ ከሆነ ግን የአጥንት መሰንጠቅ እንዲሁም ከፍተኛ የራስ ህመምም እንደሚያስከትል ይገልፃሉ።
ከማደንዘዣም ጋርም ሆነ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የማስታወስ ችግር እንዲሁም የራስ ህመም የጎንዮሽ ጉዳቶቹ እንደሆኑ ዶክተር ዮናስ ይናገራሉ።
"ጉዳቱንና ጥቅሙን አመዛዝነን ነው እነዚህን ህክምናዎችን የምናዘው፤ ሰውየው አይበላም አይጠጣም ህይወቱ አደጋ ላይ ነው፤ ስለዚህ ስለ ራስ ሀመም ሆነ ጊዜያዊ መዘንጋትን አናስታውስም የሞት አፋፍ ላይ ላለ ሰው ዋናው ነገር ህይወትን ማዳን ነው" ይላሉ።
በኤሌክትሮ ኮንቨልሲቭ ቴራፒ የታከሙ ኢትዮጵያውያን የአዕምሮ ህሙማንን ጥናቱ ያላካተተ ሲሆን በኢትዮጵያ ያሉ የአዕምሮ ህሙማን ህክምና ማዕከላት ዶክተሮች ግን የጎንዮሽ ጉዳቱን ቢረዱትም ምንም አይነት የማቆም ዕቅድ እንደሌላቸው አይተነው ይናገራል።
የተለያዩ ምርምሮችን ያካተተው ጥናቱ የናቷን ሞት ማስታወስ የማትችል ህመምተኛና በከፍተኛ ሁኔታ የአዕምሮ ጉዳት የደረሰባቸውና ዘላቂ የሆነ የመርሳት ችግር ያጋጠማቸው ብዙ እንደሆኑ ይናገራል።
በአጠቃላይም ይህንን ህክምናን "በሰው ልጅ ላይ ኢሰብአዊ የሆነ ስቃይና እንግልት" በማለት ይገልፀዋል።
በአለም አቀፍ ህክምናው ዘርፍ ቴራፒውን በመጠቀም ላይ ያለው አቋም የተከፋፈለ ሲሆን የሚቃወሙትም እንዳሉ በተቃራኒው የሞት አፋፍ ላይ የደረሱ የአዕምሮ ህሙማን የሞትና የህይወት ጉዳይ ስለሆነ ከሞት ይህንን ህክምና በመጠቀም ማዳንን ይመርጣሉ።
ከዚህ በተቃራኒው የሰብአዊ መብት ተሟጋⶇች ስቃይና እንግልት ስለሆነ መቆም አለበት ይላሉ።
"በስቃይና እንግልት መታከም ኢሰብአዊ ነው፤ ህመምተኞቹም ፈቃድ መስጠት የማይችሉበት ሁኔታ ላይ በመሆናቸው የማስታወስ ችግር ወይም የአዕምሮ ጉዳት እንደሚደርስባቸው አያውቁም"ይላል አይተነው።
ምንም እንኳን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ብለው ይህንን ቢያወግዙትም ምርጫው ግን ሞት ወይም ይህንን ህክምና ተጠቅሞ ማዳን እንደሆነ ዶክተር ዮናስ ይናገራሉ።
"ይሄ የሞራል ክርክር ነው። አንድን ሰው ቢሞት ይሻላል ወይስ ተሰቃይቶና ተንገላቶ በየትኛውም መንገድ ማትረፍ ይሻላል?" በማለት አይተነው ይጠይቃል።
መታሰርና ስቃይ
በተለያዩ የጤና ማዕከላት የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማንን ሁኔታን እንደመታሰር የሚቆጥረው አይተነው "ህሙማኑ በቤተሰብና በዘመድ ታስረው ወደ ማዕከሉ ቢመጡና ደህና ነኝ ቢሉ ተገደው ይታከማሉ ወይስ? በየጊዜው ስላለው ህክምናና ስለሚደረግላቸው ህክምና የጎንዮሽ ጉዳትስ ምን ያህል ይነገራቸዋል የሚለውን ጥያቄ ይጠይቃል?
ምንም እንኳን ፈቃድ መስጠት የማይችሉ ህመምተኞች ቢኖሩም ፈቃድ መስጠት የሚችሉ ግን መጠየቅ አለባቸው ይላል።
" ሁሉንም የአዕምሮ ህመምተኞች ዞሬ አነጋግሬቸዋለሁ ሁሉም የሚሉት ፈቃድም እንዳልተጠየቁና ስለ ህክምናቸው እንደማይነገራቸው ነው" ይላል።
በአማኑኤልም ሆስፒታልም ሆነ በገፈርሳ እጃቸውንና እግራቸውን ታስረው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች እንዳየ የሚናገረው አይተነው ""ኢ-ሰብአዊ ድርጊትም ነው" ይላል።
በገፈርሳ ከ20-30 የሚሆኑ ህሙማን በአንድ ክፍል ውስጥ የሚያድሩ ሲሆን በሚጮሁበት ጊዜ "ሌሎች ሻል ያሉ ህመምተኞች" በአንሶላ ያስሩዋቸዋል ወይ ከበር አስወጥተው እንደሚያባርሩዋቸው አቶ አይተነው ይገልፃል።
" የአዕምሮ ህሙማኑ ሌሊት ነርስም ሆነ ሀኪምም መጥራት አይችሉም፤ ስለዚህ በሚጮሁበት ጊዜ ከነሱ ሻል ያሉ የአዕምሮ ህሙማን ያስሩዋቸዋል ወይም በሌሊትም ቢሆን እንደሚያባርሩዋቸው ተመልክቻለሁ።
ይሄ ሁኔታ ደግሞ አደጋ ላይ ይጥላቸዋል።" ይላል።
ዋናው ነገር ደህንነት ነው የሚሉት ዶክተር ዮናስ "በአንዳንድ አጋጣሚዎች ህመምተኞች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው በሚደባደቡበት ወቅትና ሰው በሚያጠቁበት ወቅት ሰዎች ተቆጣጥረው ቢጥሏቸው ወይ ቢታሰሩ የአዕምሮ ህከምና ዕውቀቱ ለሌለው ሰው ስቃይና እንግልት ሊመስል ይችላል" ይላሉ።
"ደህንነት መፍጠር የማይቻል ከሆነ አስቸጋሪ ነው፤ ደህንነቱ ግን ከድህነቱና ኢኮኖሚው አንፃር ድብደባና ጥቃት ሊመስል ይችላል። ህመምተኞቹ እስከሚረጋጉ ድረስም ሊታሰሩ ይችላል። ካለበለዚያ በአካባቢው ጉዳት እንዲያደርሱ መፍቀድ ነው" ይላሉ።
በመጀመሪያም ህመምተኛውን ለማረጋጋት የሚወሰደው እርምጃ መርፌ መውጋት እንደሆነ የሚገልፁት ዶክተር ዮናስ መድሀኒቱ እስኪሰራ ሶስት ሰዓትም እንደሚወስድ ይገልፃሉ።
" በነዛ ሰዓታት ውስጥ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። ራሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መደረግ አለበት።" ይላሉ ዶክተር ዮናስ
ከዚያም በተጨማሪ የግል ህይወታቸው ሙሉ በሙሉ የተጋለጠና እንደነ ገፈርሳ ያሉት ማዕከላት ላይ ሽንት ቤት ሳይቀር በቁጥጥር ነው የሚለው አይተነው።
በገፈርሳ ማዕከል 20፣ 30 አመት የቆዩና ከማህበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትም መንገድ አልተመቻቸም ይላል። በገፈርሳ ማዕከል በተለይም ብቻቸውን መንገድ ላይ ሲሄዱ መኪና የተገጩበት፣ጫት ሲገዙም አይተነው እንደተመለከተ ይናገራል።
ክፍተት እንዳለ የሚናገሩት ዶክተር ዮናስ ይሄም መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ለተላላፊ በሽታዎች እንደ ወባና ኤችአይቪ ኤድስ ስለሆነ ነው።
በጤና ማእከላት ብቻም ችግሩ ስለማይፈታ በፀበል ቦታዎች ድብደባዎች እንዲቀሩና በጥምረትም መድሃኒት እንዲሰጣቸውና የምክር አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት እንዲሰጣቸው ማድረግ አስችሏል።
"በምዕራባውያን ሞዴል ሳይሆን በአገር በቀል ሁኔታ ህክምናው እንዲሻሻል መደረግ አለበት"ይላሉ።
ጨምረውም "በምእራባውያን አይን ሀገሪቷ መተቸት የለበትም፤ ድህነቱ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፤ በመንገድ ላይ ቆሻሻ አጥንት የሚለቅሙ አሉ እነሱን አስሮ መመገብ ምንም ችግር የለውም" ይላሉ ዶክተር ዮናስ።
ድህነትም ቢኖር የሰብአዊ መብት መጣስ ድርድር ውስጥ መግባት የለበትም የሚለው አይተነው የአዕምሮ ጤና ህግ ባለመኖሩ ክፍተትን ፈጥሯል የሚለው አይተነው በአዕምሮ ህሙማን ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የህግ ማዕቀፍም ሊኖርም ይገባል ይላል።